ባሕር ዳር:ጥቅምት 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰብሳቢነት የሚመራው፣ ሁሉም የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች እና ፡ሁለቱ ከተማ አሥተዳደር ፍርድ ቤቶች አባል የኾኑበት ሀገር አቀፍ የሕግ ተርጓሚዎች የግንኙነት መድረክ በድሬድዋ ከተማ ተካሂዷል።
በደሬድዋ ከተማ አሥተዳደር ፍርድ ቤቶች ፣ በሐረሪ እና ሶማሌ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች የተሠሩ የፍርድ ቤት ሕንፃ እድሳት እና የዲጅታላይዜሽን ሥራዎች ጉብኝትም ተካሂዷል።
በመድረኩ የተሳተፉት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው በሁሉም ፍርድ ቤቶች የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል እና ውጤታማ ለማደረግ የተሠሩ ሥራዎች አበረታች መኾናቸውን ገልጸዋል። በፌደራልም ኾነ በክልሎች ደረጃ ፍርድ ቤቶችን በሰው ኃይል ፣ በበጀት እና በቴክኖሎጅ ለማጠናከር የተሠሩ ሥራዎች ጥሩ መኾናቸውን ተናግረዋል። የፌደራል እና የክልል መንግሥታት እያሳዩ ያሉት ቁርጠኝት ከፍተኛ እውቅና ሊሰጠው የሚገባ ነው ብለዋል።
ሁሉንም ፍርድ ቤቶች ወደ ተቀራራቢ የዳኝነት የአገልግሎት አሰጣጥ ደረጃ ለማምጣት በፍርድ ቤቶች መካከል ያለው የእርስ በእርስ መደጋገፍ እና ትብብር ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ተጠናክሯል ነው ያሉት። የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የዲጅታላይዜሼን ሥራዎች በሁሉም ክልሎች እንዲስፋፋ ላደረገው ድጋፍ ሊመሰገን ይገባዋል ብለዋል ።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የጋራ መድረኩ እየተጠናከረ እንዲሄድና በየአካባቢው ካሉ መልካም ተሞክሮዎችና ተግዳሮቶች ልምድ በመውሰድ ለኅብረተሰቡ የተሻለ የዳኝነት አገልግሎት በመስጠት በፍርድ ቤት ላይ ያለውን አመኔታ ለማሳደግ እንደሚሠራ ገልጸዋል።
የግንኙነት መድረኩ የጋራ መግለጫ አውተጥቷል።
በመግለጫውም በ2013 ዓ.ም በአዋጅ ቁጥር 1231/2013 የተቋቋመው ሀገር አቀፍ የሕግ ተርጓሚዎች መድረክ በተጠናከረ ሁኔታ መደበኛ የግኙነት መድረኮችን በማድረግ ላይ ይገኛል ተብሏል።
መድረኩ ነጻ፣ ገለልተኛ እና የሕዝብ አመኔታን ያተረፈ የዳኝነት አካልን በመገንባት ፍርድ ቤቶች በዲሞክራሲ ግንባታ እና በሀገር እድገት ላይ ያላቸውን ሚና የሚያጎለብት ነው፡፡
ይህ መድረክ ፍርድ ቤቶች ድንበር የለሽ የኾነዉን ፍትሕን ለማስፈን በመተባበር፣ የጋራ ጉዳዮች ላይ በመምከር፣ የመፍትሔ አቅጣጫን በመጠቆም እና ሊስፋፋ የሚገባ መልካም ተሞክሮዎችን በማጋራት የዳኝነት አካሉ አገልግሎት አሰጠጥ የሚገባዉ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ያግዛል። ኢትዮጵያ የፌዴራል ሥርዓትን የምትከተል ሀገር በመኾኗ በፌዴራልና በክልል ደረጃ ሕጎች በሚወጡበትም ኾነ በሚተረጎሙበት ወቅት የፌዴራሊዝምን መሠረታዊ ጽንሰ ሃሳብ የተከተለ እንዲኺን ለማድረግ መድረኩ አይተኬ ሚና ይኖረዋል ነው የተባለው።
ሀገር አቀፍ የሕግ ተርጓሚዎች ግንኙነት መድረክ የሚከተሉትን ውሳኔዎችና የአቋም መግለጫዎችንም አሳልፏል፡፡

ከሁሉም በላይ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና በክልል ፍርድ ቤቶች፣ የክልል ፍርድ ቤቶች የእርስ በእርስ ትብብር እና ድጋፍ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መሄዱንና በፍርድ ቤቶች መካከል ከፍትኛ የኾነ የትብብር መንፈስን የፈጠረ ፤ እንደ ሀገር ጠንካራ የዳኝነት ሥርዓት ለመገንባት የተያዘውን ርዕይ ለማሳካት በሚደረገዉ ጥረት ከፍተኛ አቅም እየኾነ የመጣ መኾኑ በመድረኩ የጋራ ግንዛቤ ተይዞበታል።

የፍርድ ቤቶችን የበጀት እና የሰዉ ሃብት አሥተዳደር ነጻነትን በማረጋገጥ ረገድ በአብዛኛዉ አካባቢዎች የታየዉ መሻሻል፣ የፌዴራል እና የክልል መንግሥታት የዳኝነት አካሉን ለማጠናከር ያሳዩት ቁርኝነት ሊበረታታ እና እውቅና ሊሰጠው የሚገባው መኾኑን።

በፌዴራልና በክልል ፍርድ ቤቶች የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ያለው፣ ተደራሽ፣ ግልጽ እና ወጭ ቆጣቢ ለማድረግ የተጀመሩ የዲጅታላይዜሽን ሥራዎች ፤ ሁሉንም የሀገሪቱ ፍርድ ቤቶች አገልግሎት አሰጣጥ ወደ ተቀራራቢ ደረጃ ለማምጣት እየተሠራ ያለው ሥራ በአብዛኛዉ አካባቢዎች አበረታች ነው። በዚህ ረገድ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለክልል ፍርድ ቤቶች እያደረገ ያለው ድጋፍ እውቅና ሊሰጠው የሚገባ ነው።

አመራጭ የሙግት መፍቻ ሥርዓቶችን በተለይም ባሕልዊ ፍርድ ቤቶችን በየአካባቢዉ ለማቋቋምና ለማጠናከር የተሠሩ ሥራዎች አበረታች መኾናቸው ቀጣይነት ያለው ክትትል እና ድጋፍ የሚያስፈልግ መኾኑን።

ጊዜዉ የሚጠይቀውን የዳኝነት አገልግሎት ለመስጠት ቴክኖሎጂን መጠቀም ለምርጫ የሚቀርብ ጉዳይ ባለመኾኑ የክልልም ሆነ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ተገቢነት ያላቸውን ልምዶች በመቀመር እና በማስፋፋት ቀልጣፋ፣ ጥራት ያለዉ እና ተደራሽ የኾነ አገልግሎት ለመስጠት ፍርድ ቤቶች ከምን ጊዜዉም በላይ በላቀ ሁኔታ መሥራት እንደሚገባቸዉ ከስምምነት ተደርሷል፡፡

በባለፈዉ የግንኙነት መድረክ በተቀመጠ አቅጣጫ መሠረት በተወሰኑ ክልሎች የዳኞቸ ያለመከሰስ መብት በክልሉ ሕግ ማዕቀፍ ውስጥ ለመግባታቸው ትልቅ እውቅና እንሰጣለን። አሁንም ችግሩ ሙሉ በሙሉ ባለመቀረፉ የዳኞች ያለመከሰስ መብት በሕገ መንግሥቱ ላይ በተቀመጠ መርሕ መሠረት ተግባራዊ ባልተደረገባቸው ጥቂት ክልሎች የሕግ ማዕቀፍ እንዲኖር።

ፍርድ ቤትች በሰው ኃይል፣ በበጀት እና በቴክኖሎጅ በመደገፍ በሕገ መንግሥት የተሰጣቸውን ተልዕኮ በአግባቡ በመወጣት ለሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት፣ ለሕግ የበላይነት እና ሰባዊ መብቶች አከባበር መዳበር የበኩላቸዉን የማይተካ አስተዋፅኦ ማበርከት ይችሉ ዘንድ በቂ በጀት እንዲያገኙ የሚመለከተዉ አካል ሁሉ ኃላፊነቱን እንዲወጣና የበኩሉን ትብብር እንዲያደርግ።

የጋራ በኾኑ እና እንደ ሀገር ለውጥ ሊያመጡ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ጋራ ፕሮጄክቶች ተቀርጸው ተግባራዊ እንዲደረረጉ አቅጣጫ የተቀመጠ መኾኑን።

የግንኙነት መድረኩ ከዚህ በፊት በሰጠዉ አቅጣጫ መሠረት በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 79(7) መሠረት ለክልል ፍርድ ቤቶች ማካካሻ በጀት ስለሚሰጥበት ቀመር ላይ ተወያይቶ እንደ መስፈርት ከቀረቡ ጉዳዮች በተጨማሪ ሌሎች መስፈርቶች እንዲካተቱና ለቀጣይ ዓመት በጀት ክፍፍል አተገባበር መመሪያ ተዘጋጅቶ እንዲመጣ አቅጣጫ አስቀምጧል።

የኢፌዴሪ ሀገር አቀፍ የሕግ ተርጓሚዎች ግንኙነት አሠራር ሥርዓትን ለመዘርጋት በወጣ መመሪያ ቁጥር 01/2016 አንቀጽ 22 መሠረት የሕግ ተርጓሚዎችን የግንኙነት መድረክ የሚያስተባብር ጽሕፈት ቤት የተቋቋመ ቢኾንም ጽሕፈት ቤቱ ተጠናክሮ በሚያስፈልገዉ ሁሉ እስኪደራጅ ድረስ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መዋቀር ውስጥ ባለው አደረጃጀት የማስተባበር ሥራዎች እንዲቀጥሉ መድረኩ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

ቀጣይ የሚካሄደዉ ሀገር አቀፍ የሕግ ተርጓሚዎች መድረክ በቤኒሻንጉል ክልል እንዲካሄድ፣ የግንኙነት መድረኩን በምክትል ሰብሳቢነት ሲመሩ የነበሩት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት ኤርሳኖ አቡሬ የኃላፊነት ዘመን ማብቃትን ተከትሎ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደዉ ቀጣዩ የትብብር መድረኩ ምክትል ሰብሳቢ ኾነው እንዲሠሩ በጋራ በመወሰን መድረኩ መጠናቀቁን ከአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
የሀገር አቀፍ የሕግ ተርጓሚዎች የግንኙነት መድረክ ተሳታፊ ፍርድ ቤቶች ከላይ የተጠሰውን የጋራ አቋም የያዝን ሲኾን ተጠያቂነት የሰፈነበት፣ ቀልጣፋ፣ ጥራት ያለውና ተደራሽ የኾነ የዳኝነት አገልግሎት በመስጠት የሕዝብ አመኔታ የተቸረዉ የዳኝነት አካል እንዲኖር ለማድረግ እንደገና ቃላችንን እናድሳለን ብለዋል በአቋም መግለጫቸው።