የፖሊዮ ክትባት ዘመቻው ውጤታማ ኾኖ ተጠናቅቋል።

4
ባሕር ዳር: ጥቅምት 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ‎በዘመቻ ሲሰጥ የነበረው የፖሊዮ ክትባት ውጤታማ ኾኖ መጠናቀቁን በአማራ ክልል የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታውቋል፡፡
‎በአማራ ክልል የፖሊዮ በሽታ በደቡብ ጎንደር ዞን አንዳቤት ወረዳ እና ጎንደር ከተማ አሥተዳደር በመገኘቱ ለወረርሽኝ ምላሽ ለመስጠት ከመስከረም 30 እስከ ጥቅምት 3/2018 ዓ.ም ድረስ በዘመቻ ክትባት መሰጠቱ ይታወሳል፡፡
‎ክትባቱ በሽታው በተገኘባቸው እና አጎራባች በኾኑ አካባቢዎችም ተሰጥቷል፡፡ ጎንደር፣ ደብረ ታቦር፣ ባሕር ዳር እና ደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደሮች፣ ማዕከላዊ ጎንደር፣ ደቡብ ጎንደር፣ ሰሜን ጎጃም እና ምሥራቅ ጎጃም ዞኖች ክትባቱ የተሰጠባቸው ቦታዎች ናቸው፡፡
በእነዚህ ዞኖች በ58 ወረዳዎች ክትባቱ መሰጠቱን ከአማራ ክልል የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
‎በኢንስቲትዩቱ የበሽታዎች እና የጤና ሁኔታዎች ቅኝት እና ምላሽ ቡድን አሥተባባሪ ፅጌረዳ አምሳሉ ክትባቱ በታቀደው ልክ መፈጸሙን ተናግረዋል፡፡
‎በክልሉ ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ዕድሜያቸው ከ10 ዓመት በታች ለኾኑ ሕጻናት ክትባቱን ለመስጠት በዕቅድ ተይዞ 3 ሚሊዮን 591 ሺህ 778 ሕጻናት መከተባቸውን ገልጸዋል፡፡
‎የክትባት ዘመቻው ውጤታማ የኾነው ለክትባቱ አስፈላጊው የቅድመ ዝግጅት ሥራ በአግባቡ በመሠራቱ ነው ብለዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል ለሥራው የሚኾኑ ኮሚቴዎችን ቀደም ብሎ በማዋቀር በየጊዜው እየተገመገመ በመከናወኑ እንደኾነ ነው የገለጹት፡፡
‎ለዘመቻ ሥራው አስፈላጊ ግብዓቶች ጊዜያቸውን ጠብቀው በአግባቡ እንዲደርሱ መደረጉንም ገልጸዋል፡፡ የክትባት መድኃኒቶች ወደ ጤና ተቋማት በተገቢው ሁኔታ መድረሱንም ተናግረዋል፡፡
በክትባት ሥራው ላይ የተሳተፉ የጤና ባለሙያዎች፣ አሥተባባሪዎች እና ሌሎች ለሚመለከታቸው አካላትም ቀደም ብሎ አስፈላጊው ሥልጠና መሰጠቱን አንስተዋል፡፡
‎በዘመቻው ወቅት ያጋጠሙ ችግሮችን በተመለከተ አንዳንድ ወላጆች እና አሳዳጊዎች በግንዛቤ ችግር አናስከትብም የሚሉ ነበሩ፡፡ ይህንንም ባለሙያዎች የማስገንዘብ ሥራዎችን በመሥራት ልጆች እንዲከተቡ መደረጉን ነው የገለጹት፡፡
‎አሥተባባሪዋ የፖሊዮ ክትባት ለረጅም ዓመታት ሲሰጥ የቆየ በመኾኑ ኅብረተሰቡ ክትባት ሲሰጥ በፈቃደኝነት ልጆቻቸውን እንዲያስከትቡ፤ መረጃ ሲፈልጉም የጤና ባለሙያዎችን በመጠየቅ መረዳት እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡
በፖሊዮ ክትባት ዘመቻው ትብብር ላደረጉ አካላትም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
‎ዘጋቢ፡- ፍሬሕይዎት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየጎንደር ከተማን ሰላም እና ልማት የማረጋገጥ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል።