
ጎንደር፡ ጥቅምት 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ከተማ አሥተዳደር የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የፓርቲ እና የመንግሥት ተግባራት አፈጻጸም ግምገማና የቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ውይይት አካሂዷል።
በውይይቱ አሁናዊ የሰላም ሁኔታዉ የተረጋጋ እንዲኾን የብሎክ አደረጃጀቶችን ማጠናከር መቻሉ፣ በከተማዉ የተጀመረው የኮሪደር ልማት ተጠናክሮ እንዲቀጥል መደረጉ እና በየክፍለ ከተሞች የሰነድ አየያዝ በተሻለ ሁኔታ መጠናከሩ ተጠቅሷል።
ባለፉት ዓመታት የተፈጠረዉ የሰላም እጦት ለሥራ እንቅፋት ፈጥሮ እንደነበር ያነሱት የውይይቱ ተሳታፊዎች የሰላም እጦቱ ሳይገድባቸዉ የተጀመሩ ሥራዎች በተያዙት ልክ እንዲቀጥሉ መደረጉ የሚበረታታ መኾኑንም ተናግረዋል።
የዕቅዶች በተዋረድ ካለዉ ዕቅድ ጋር ተናባቢ አለመኾን እና የሥራ እድል ፈጠራው በሚጠበቁ ልክ አለመኾን በውስንነት ተነስተዋል።
በትምህርት ቤቶች በቂ ቁሳቁስ እና የመማሪያ ክፍሎች ጥራት አለመኖር ለመማር ማስተማር እንቅፋት ፈጥሮ መቆየቱንም ተናግረዋል።
አገልግሎት አሠጣጡን ለማዘመን እየተሠራ ያለዉ ተግባር የሚበረታታ ነው ያሉት ታሳታፊዎቹ የነበሩ ጉድለቶችን በመቅረፍ የተሻለ ተግባር ለመፈጸም መሠራት እንደሚገባ አመላክተዋል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸዉ ዳኘዉ የጸጥታ ኃይሉን በማጠናከር ዘላቂ ሰላምን የማስፈን ሥራ በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል።
በቀጣይ ወራት የኢንቨስትመንት፣ የቱሪዝም ዘርፉን እና የሥራ እድል ፈጠራን ማሳደግ ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሠራም አንስተዋል።
የትምህርት እና የጤና ዘርፉን ለማዘመን የሥራ ኀላፊዎች እና ባለድርሻ አካላት በትኩረት እንዲሠሩም አሳስበዋል።
የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኀላፊ በሪሁን መንግሥቱ ጎንደር ከተማ ላይ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ የመሪዎች እና የሕዝቡ ቅንጅትና ቁርጠኝነት የሚበረታታ ነዉ ብለዋል።
የሰላሙ ባለቤት ሕዝቡ እዲኾን እየተሠራ ያለው ተግር ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ መኾኑንም ተናግረዋል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አሥተባባሪና የአማራ ክልል ከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር) ተጀምረው ያልተጠናቀቁ ግንባታዎች በተያዘላቸዉ ጊዜ እንዲጠናቀቁ ክትትል ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል። የመሪዎችን የመፈጸም አቅም ማሳደግ እንደሚገባም አንስተዋል።
የተያዘዉን ተግባር አጠናክሮ ማስቀጠል፣ የተጀመሩ የጸጥታ፣ የልማት፣ መልካም አሥተዳደር ሥራዎች ማስፋት እና መደገፍ በቀጣይ ሊሠሩ የሚገባቸው ተግባራት መኾን እንደሚገባቸዉም አስገንዝበዋል።
በሩብ ዓመቱ የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ተቋማት የዕውቅና እና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።
ዘጋቢ:- አዲስ አለማየሁ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!