
አዲስ አበባ: ጥቅምት 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ እና በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሠሩ የከባድ መኪኖችን በኢትዮጵያ ለመገጣጠም የሚያስችል ስምምነት ተካሔደ።
ቢአኤካ ግሩፕ ከቻይናው የካባድ መኪና ቀዳሚ አምራች ከኾነው እና ከግዙፉ ሻክማን ኩባንያ ጋር ነው ይህንን ተግባር ያስተዋወቁት። ስምምነቱ የተከናወነውም የኢትዮ ቻይና የቢዝነስ ፎረም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ባለበት ሰዓት ነው።
በፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ (LNG) እና በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሠሩ (EV) የከባድ መኪኖች በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው በቢአኤካ ግሩፕ የተዋወቁት።
የቢአኤካ ግሩፕ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሚካኤል ካሳ ስምምነቱ በመጀመሪያው ዙር ብቻ 1 ሺህ 500 መኪኖችን ገጣጥሞ ማቅረብ የሚያስችል ስምነት ነው ብለዋል። አሁን ላይ ደግሞ በቀጥታ 150 መኪኖች ታዘው በሂደት ላይ መኾናቸውንም ገልጸዋል።
ይህንን ተከትሎ ቻይና ሀገር የሚገኘው የሻክማን የመኪና አምራች ብቸኛ የኢትዮጵያ ወኪል የኾነው እና ከዚህ ቀደም የሻክማንን የደረቅ፣ የፈሳሽ እንዲሁም የኮንስትራክሽን ከባድ መኪኖችን ወደ ሀገራችን በማስመጣት የሚታወቀው ቤአኤካ በኢትዮጵያ ለመገጣጠም የሚያስችል የፋብሪካ ግንባታ በማጠናቀቅ አዲስ ነገር አስተዋውቋል ብለዋል።
ይህ ፕሮጀክት በኢትዮጵያ ከፍተኛ የኾነ የኢነርጅ ሽግግርን የሚያመጣ ቁልፍ ጅማሮ ተደርጎ የሚወሰድ እንደኾነም ገልጸዋል። ቢአኤካ በሚቀጥሉት ጥቂት ጊዜያት ኢትዮጵያ ውስጥ በአማራጭ ኃይል እንዲሁም በታዳሽ ኃይል የሚንቀሳቀሱ ከባድ ተሽከርካሪዎችን እውን ያደርጋል ብለዋል።
የሻንሽ አውቶሞቢል ግሩፕ (ሻክማ) ዋና ሥራ አሥኪያጅ ዣው ሽያንግሻንግ በበኩላቸው በቻይና በከባድ መኪና መገጣጠም እና አቅርቦት ቁጥር አንድ መኾናቸውን ገልጸዋል። ካምፓኒያቸው ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ30 ዓመት በላይ በኢትዮጵያ ጨምሮ በአፍሪካ መሰል ምርት የማቅረብ ልምድ ያለው በመኾኑ ይህ ስምነት ያለምንም ችግር ይከናወናል ብለዋል።
ጥራት ያላቸው ምርቶችን በአግባቡ እና በጊዜ በማቅረብ ለሀገሪቱ ሥራ ፈጠራ እና ሎጅስቲክስ አቅርቦት የበኩላችንን እንወጣለን ብለዋል። የአፍሪካ የገበያ ድርሻው ከድርጅቱ ዓመታዊ ሽያጭ ውስጥ 45 በመቶ እንደሚሸፍንም ገልጸዋል።
በቅርቡ በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል ውስጥ የተበሰረውን የካሉብ የተፈጥሮ ጋዝ የመጀመሪያ ዙር ማምረቻን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) መጭው ጊዜ በፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ የሚሠሩ መኪኖች ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡበት ሥርዓት እንደሚዘረጋ የፖሊሲ አቅጣጫ መስጠታቸው ይታወሳል።
ዘጋቢ:- አንዷለም መናን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!