ዘመናዊ የባቡር መስመሮችን በመዘርጋት ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት እየተሠራ ነው።

6
አዲስ አበባ: ጥቅምት 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የመጀመሪያውን ብሔራዊ የቢዝነስ እና ኢንቨስትመንት ጉባኤ እያካሄደ ነው።
የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አሥፈፃሚ ኢንጂነር ህሊና በላቸው ኮርፖሬሽኑ ዘመናዊ የባቡር መስመሮችን በመዘርጋት የተሞች የሕዝብ ለሕዝብ ትስስሮችን ለማጠናከር እና ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት እየተሠራ ነው ብለዋል።
ጉባኤውም በዘርፉ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ እና አልሚ ባለሃብቶችን ለመሳብ እንዲሁም የፋይናንስ ድጋፎችን በማፈላለግ በአጋርነት ለመሥራት አስቻይ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ያለመ መኾኑን ጠቁመዋል።
የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ድኤታ ዳንጌ ቦሩ በሎጅስቲክስ ሥርዓቱ ላይ የባቡር ጭነት አገልግሎት ትልቁን ድርሻ እንደሚይዝ ገልጸው ጊዜን እና ወጭን ከመቆጠብ አንጻርም ትልቅ ሚና አለው ብለዋል።
ኢትዮጵያም በዘርፉ ያላትን ተደራሽነት ለማጠናከር ከአፍሪካ የዘለለ ዓለም አቀፍ ተቋም ያስፈልጋታል ነው ያሉት።
ይህንን ለማሳካትም የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የጀመረውን ጉዞ ለማጠናከር ምቹ እና አስቻይ የኢንቨስትመንት ምህዳርን መፍጠር እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።
የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር የፖሊሲ እና የሪፎርም ማሻሻያዎችን በማድረግ ለግሉ ዘርፍ ክፍት እንዲኾን እየተደረገ መኾኑንም አንስተዋል።
በአፍሪካ ኅብረት የመሠረተ ልማት እና ኀይል ኮሚሽነር ሌራቶ ማታቦጅ በኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ከሀገሪቱ አልፈው የአህጉሪቱን እና የቀጣናውን ዕድገት ለማሳለጥ ትልቅ አስተዋጽኦ አላቸው ብለዋል።
ደረጃቸውን የጠበቀ የመሠረተ ልማት ሥራዎችን ለመዘርጋትም ግዙፍ መዋለንዋይን ይጠይቃል ያሉት ኮሚሽነሯ ይህንን ተረድቶ በትብብር መሥራት እና እርስ በእርስ መተሳሰርን ለማጠናከር ኅብረቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ተናግረዋል።
በጉባኤው ላይ በዘርፉ የተሰማሩ አጋር እና ባለድርሻ አካላትም ተሳትፈዋል።
ዘጋቢ፦ ቤተልሄም ሰለሞን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየአርሶ አደሮች ቴክኖሎጅን የመጠቀም ፍላጎት ጨምሯል።
Next articleየቻይና ቴክኖሎጂ እና ፈጠራን ከኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሃብት ጋር በማስተሳሰር ለጋራ ልማት መሥራት ይገባል።