
ባሕር ዳር: ጥቅምት 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የብልጽግና ፓርቲ የ2018 በጀት ዓመት አንደኛ ሩብ ዓመት የፓርቲ ሥራዎች አፈጻጸም ግምገማ መድረክ ማካሄድ ጀምሯል።
ከዛሬ ጀምሮ ለሁለት ተከታታይ ቀናት በዋናው ጽሕፈት ቤት እየተካሄደ በሚገኘው መድረክ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንትና የዋና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አደም ፋራህን ጨምሮ ሌሎች የፓርቲው ከፍተኛ መሪዎች ተገኝተዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት እና የዋና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አደም ፋራህ ፓርቲው በሁሉም ዘርፎች እና መስኮች ስኬታማ ጉዞ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
ለኢትዮጵያ እና ለፓርቲው በሚመጥን መንገድ ከፍ ተደርጎ በመታቀዱ፤ በመደመር እሳቤ ሁሉንም አቅሞች ለመጠቀም ጥረት በመደረጉ፤ በፕራግማቲክ እይታ በየአካባቢው ያለውን ተግባራዊ እውነታ መሠረት በመደረጉ፤ በፍጥነትና በፈጠራ መርሕ በመሠራቱ እና ፈተናን ወደ ዕድል የመቀየር መርሕ መከተል በመቻሉ ፓርቲው ዘርፈ ብዙ ስኬቶችንና ድሎችን አስመዝግቧል ነው ያሉት።
በመድረኩ በፓርቲው እና በሕዝብ ንቅናቄ የተሠሩ ሥራዎች በጥልቀት ይገመገማሉ ተብሏል። በሁሉም መስኮች የተመዘገቡ ስኬቶችን ማስቀጠል እና ጉድለቶችን ለማረም የጋራ መግባባት ይፈጠራል ተብሎ እንደሚጠበቅም ከብልጽግና ፓርቲ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!