ባሕር ዳር: ጥቅምት 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢንስቲትዩቱ ቦርድ ሁለተኛ መደበኛ ሥብሠባዉን በማከናወን በመጀመሪያዉ መደበኛ ጉባኤ የተላለፉ ውሳኔዎች እና አቅጣጫዎችን አፈጻጸም ከገመገመ በኋላ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ በመወያየት ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት እና የኢንስቲትዩቱ የቦርድ ሰብሳቢ ዓለምአንተ አግደዉ የአማራ ክልል የፍትሕ እና ሕግ ኢንስቲትዩት በአዋጅ ቁጥር 299/2017 ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተጠሪ ኾኖ እና አዳዲስ ኀላፊነቶች ተሰጠውት እንደገና ከተቋቋመ በኋላ የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
በክልሉ የሕግ እና ፍትሕ ጉዳዮች የልህቀት ማዕከል ኾኖ እና ዓለምአቀፍ ተወዳዳሪነት ያለው ተቋም ኾኖ እንዲገነባ የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውንም አንስተዋል። ለዚህ የሚኾን ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱን እና እስከ አሁን የተሠሩ ሥራዎችም አበረታች መኾናቸዉን ጠቅሰዋል።
ቦርዱ የሚያስተላልፋቸዉ ስትራቴጂክ ውሳኔዎች እና የሚሰጠዉ ድጋፍ ይህንን ተሳቢ ያደረገ መኾን እንዳበትም ገልጸዋል።
የአማራ ክልል የፍትሕ እና ሕግ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ደሴ ጥላሁን (ዶ.ር) ኢንስቲትዩቱ የሠራቸውን ሥራዎች በተመለከተ ማብራሪያ አቅርበዋል።
ከአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው በቀረበው ማብራሪያ ላይ ሰፊ ውይይት ከተደረገ በኋላ ቦርዱ በሚከተሉት ጉዳዮች ላይ ውሳኔዎችን እና አቅጣጫዎችን አስቀምጧል፡፡

የኢንስቲትዩትን የ2017 በጀት ዓመት የ12 ወራት የዕቅድ አፈጻጻም ሪፖርት ላይ ተወያይቶ ኢንስቲትዩቱ እንደገና ከተቋቋመ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የተሠሩ ሥራዎች ውጤታማ እና ተቋሙን በለውጥ ሂደት ላይ የሚያሳይ መኾኑን በመገምገም ሪፖርቱን አጽድቋል።

የኢንስቲትዩት የ5 ዓመት ስትራቴጅክ ዕቅድ ላይ ውይይት በማድረግ እና ግብዓቶችን በማከል አጽድቋል፤ የኢንስቲትዩቱን የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድም አጽድቋል።

ከኢንስቲትዩቱ የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ጋር በተጣጣመ ሁኔታ የተዘጋጀውን የፕሮጀክት ዕቅድ በማጽደቅ ተጨማሪ ሃብት የማፈላለግ ሥራዎች ላይ አቅጣጫ አስቀምጧል።

በኢንስቲትዩቱ እንደገና ማቋቋሚያ አዋጅ መሠረት የተቋሙ አደረጃጀት መዋቅር ጥናት እንዲጠና በመወሰን ይህንን የሚያከናውን ኮሚቴ ሰይሟል።

ኢንስቲትዩቱ የተሰጠውን ተልዕኮ በሚመጥን እና ተግባርና ኀላፊነቱን በአግባቡ መወጣት የሚችልበትን ምቹ ኹኔታ ለመፍጠር አዲስ ሕንጻ ለመገንባት በተያዘዉ ዕቅድ መሠረት የዲዛይን፣ የቦታ ዝግጅት እና የበጀት ጥያቄዎች በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቁ እና ወደ ሥራ እንዲገባ አቅጣጫ አስቀምጧል።

የቦርዱ የስብሰባ ሥነ ስርዓት መመሪያ ላይ ተወያይቶ አጽድቋል።

የኢንስቲትዩቱ መሪዎች፣ አሠልጣኞች እና ተመራማሪዎች የደረጃ የዕደገት እና እርከን መሰላል መመሪያ ላይ ተወያይቶ አጽድቋል።

የኢንስቲትዩቱ መሪዎች፣ አሠልጣኞች እና ተመራማሪዎች የጥቅማጥቅም መመሪያ ላይ ተወያይቶ አጽድቋል።

የመካከለኛ ጊዜ የሥራ ላይ ሥልጠና የሠልጣኞች ክፍያና ወጪ አሸፋፈን ረቂቅ የውሳኔ መነሻ ላይ ተወያይቶ አጽድቋል።

በተጨማሪም አዲስ የ18ኛ ዙር ሠልጣኝ ዳኛ እና ዐቃቤ ሕግ ምልመላ ግልጽ የምልመላ መስፈርቶች ወጥተው እንዲሠራ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ሥብሠባውን አጠናቅቋል።