“የመጻሕፍት አቅርቦት ዝግጅት ተጠናቅቋል” ትምህርት ቢሮ

1

ባሕር ዳር: ጥቅምት 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ለትምህርት ጥራት አንዱ ግብዓት መጽሐፍ ሲኾን የመጽሐፍ ተማሪ ጥምርታን አንድ ለአንድ ማድረግ ደግሞ የመንግሥት ዋና ተግባር ነው፡፡

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮም በ2018 የትምህርት ዘመን የተማሪ መጽሐፍ ጥምርታን በማሻሻል ለትምህርት ጥራት እንደሚሠራ መግለጹን አሚኮ መዘገቡ ይታወሳል፡፡

በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) የመማሪያ መጻሕፍትን በማሳተም ጥምርታውን አንድ ለአንድ ለማድረግ ታቅዶ እየተሠራ መኾኑን ገልጸው ነበር፡፡

ይህን ሃሳብ ይዞ አሚኮ ዲጅታል በትምህርት ቤቶች የመጻሕፍት አቅርቦቱ ምን እንደሚመስል ዳሰሳ አድርጓል፡፡

በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር በሽምብጥ ትምህርት ቤት ባደረገው ምልከታም የዚህ ዘገባ ቃለ መጠይቅ እስከተሠራበት ቀን ድረስ የመማሪያ መጻሕፍት በጥምርታው መሠረት ለተማሪዎች አልደረሰም፡፡

የሽምብጥ የመጀመሪያና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ምክትል ርእሰ መምህር ጋሻው ጥሩነህ በትምህርት ቤታቸው የመጻሕፍት እጥረቱ ከፍተኛ መኾኑን ገልጸዋል፡፡

ለ2018 የትምህርት ዘመን እስካሁን የቀረበ መጽሐፍ አለመኖሩንም አንስተዋል፡፡ የመጽሐፍ ጥምርታውም ከ1 ለ6 ተማሪ በላይ መኾኑን ጠቅሰዋል፡፡

ትምህርት ቤቱ ከሌሎች ትምህርት ቤቶች የሚመጡ ተማሪዎችን እየተቀበለ በመኾኑ ለመጽሐፍ ተማሪ ጥምርታው አለመጣጣም ተጨማሪ ምክንያት መኾኑንም ምክትል ርእሰ መምህር ጋሻው አንስተዋል፡፡

የብጹዕ አቡነ በርናባስ ቤዛ ብዙኀን አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሥራ አስኪያጅ መምህረሰላም አሰግድ በረደድ ዘንድሮ ለትምህርት ቤታቸው መጻሕፍት እንዳልደረሰ ጠቅሰው ከቀረበ ለመውሰድ ዝግጁ መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ሙሉዓለም አቤ (ዶ.ር) ለ2018 የትምህርት ዘመን መቅረብ ያለበት መጽሐፍ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ድረስ አለመቅረቡን ጠቅሰዋል፡፡

ትምህርት ቤቶችም እየተጠቀሙ ያሉት ባለፈው ዓመት በተሰራጨው መጽሐፍ መኾኑን አንስተዋል፡፡

የግል ትምህርት ቤቶች አንደኛ ደረጃዎቹ አስፈላጊውን ክፍያ ሲፈጽሙ መጽሐፍ እንደሚቀርብላቸውም ገልጸዋል፡፡ የሁለተኛ ደረጃዎቹ ደግሞ ከትምህርት ሚኒሥቴር መኾኑን ጠቁመው ትምህርት መምሪያው እና ትምህርት ቢሮ እንደሚያመቻቹ ነው የገለጹት፡፡

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኀላፊ እየሩስ መንግሥቱ የ2018 ትምህርት ዘመን የመጻሕፍት አቅርቦት ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡

ባለፈው የትምህርት ዓመት ከአምስተኛ ክፍል በላይ አካዳሚክ የኾኑ የትምህርት ዓይነቶችን 1ለ1 ለማድረስ ጥረት መደረጉንም ጠቅሰዋል፡፡

ከአንደኛ እስከ አራተኛ ክፍል የሁሉም መጻሕፍት እጥረት መኖሩን ጠቅሰው ዘንድሮ ይህንን ችግር ለመቅረፍ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡

በክልሉ 3 ነጥብ 6 ሚሊዮን እና በፌደራል መንግሥት 4 ሚሊዮን መጻሕፍትን ለማሰራጨት ታቅዶ እየተሠራ መኾንም ጠቅሰዋል፡፡

በክልሉ የሚታተመው መጽሐፍ ታትሞ መጠናቀቁን እና እንዲሰራጭ ማረጋገጫ መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡ ስርጭቱ በአጭር ጊዜ እንደሚከናወንም ተናግረዋል።

ለሥራው ስኬታማነትም ቢሯቸው በትብብር እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡

የግል ትምህርት ቤቶችም መጻሕፍት ተመድቦላቸው እንደሚወስዱ ነው የገለጹት፡፡ ለዚህም ቢሮው ክትትል ያደርጋል ብለዋል፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚቀርቡ መጻሕፍትም ለክልሉ እንደደረሱ እንደሚሰራጩ ገልጸዋል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“ዓባይ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ የክልሉን ኢኮኖሚ ለማሻገር እና የፋይናንስ ችግር ለመፍታት ቁልፍ ተቋም ነው” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን(ዶ.ር)
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ( ዶ.ር) የወልመል ወንዝ መስኖ ልማት ፕሮጀክትን መርቀው ሥራ አስጀመሩ።