የትራምፕ እና ፑቲን የቡዳፔስት ቀጠሮ

34
ባሕር ዳር: ጥቅምት 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ትናንት በጣም ፍሬያማ ሲሉ የገለጹትን ረጅም የስልክ ንግግር ከፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር ካደረጉ በኋላ በሩሲያ – ዩክሬን ጦርነት ላይ ለመወያየት በሃንጋሪዋ ከተማ ቡዳፔስት እንደሚገናኙ ገልጸዋል።
ትራምፕ በትሩዝ ማኅበራዊ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት ‘ክብረ ነክ’ ሲሉ የገለጹትን ጦርነት እንዲያበቃ ማድረግ ይቻል እንደኾነ ለመነጋገር በሃንጋሪዋ ቡዳፔስት ከፑቲን ጋር የሚገናኙ መኾኑን አስታውቀዋል።
በመሪዎች መካከል የተደረገው የስልክ ውይይት ለሁለት ሰዓት ተኩል ያህል የቆየ ነው። ውይይቱ በሩሲያ ጥያቄ መሠረት የተካሄደ መኾኑም ተገልጿል። ምክክሩ ከሁለት ሳምንት በኋላ እንደሚደረግም ተጠቁሟል፡፡
ከዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ዘለንስኪን ጋር ደግሞ ዛሬ እንደሚገናኙ እና በቆይታቸውም ከፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር ስለተነጋገሩባቸው ነጥቦች እና ሌሎችንም ጉዳዮችም እንደሚወያዩ ትራምፕ ገልጸዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ትራምፕ በትሩዝ ገጻቸው እንደገለጹት ከሃንጋሪው የውይይት ቀጠሮ በተጨማሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ የሚመሩት ከፍተኛ ልዑክ በሚቀጥለው ሳምንት ከሩሲያ ባለሥልጣናት ጋር ለመገናኘት እንዳቀዱ እና የሚገናኙበት ቦታ ወደ ፊት የሚገለጽ መኾኑን ተናግረዋል፡፡
የትራምፕ እና የፑቲንን የስልክ ውይይት ተከትሎ የሃንጋሪው ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦርባን ባወጡት መግለጫ በቀጠሮ ለተያዘው የሰላም ምክክር ዝግጅቶች እየተከናወኑ ነው ብለዋል። በኤክስ ማኅበራዊ ገጻቸው ላይም “ሃንጋሪ የሰላም ደሴት ናት” የሚል ጽሑፍ አስፍረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እየተወሰደ ነው።
Next articleበአጀንዳ ማሰባሰቡ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በንቃት ተሳትፈዋል።