
ባሕር ዳር: ጥቅምት 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ጋንግሪን አንድ የሰውነት ክፍል ደም አጥሮት ምግብ እና ኦክስጅን አልደርሰው ብሎ ከሙሉ አካላችን ተለይቶ እየሞተ ወይም በድን እየኾነ መምጣት ማለት ነው፡፡
አቶ በላይነህ መኮነን በጋንግሪን በሽታ ተጠቂ የኾኑ ግለሰብ ናቸው። ይህ በሽታ ሲይዘኝ መጀመሪያ ትንሽ ነፍሳት ነበር የነከሰኝ ከዛም ቁስለቱ በፍጥነት አመርቅዞ ወዲያውኑ ነበር ቁስሉ የበረታብኝ ሲሉ ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል ።
ከበፊት የስኳር ሕመም ያለብኝ መኾኑ ቁስለቱ ወደ ሌላ ነገር እንዳይቀየርብኝ ቶሎ ለመዳን ብየ ወደ ሕክምና ተቋም ሄድኩ የሚሉት ባለታሪካችን ነገር ግን ከሐኪሞች የመጣ ሃሳብ አስደነገጠኝ ይላሉ። ቁስለቱ የጀመረኝ አውራ ጣቴ ላይ ስለነበር የእግሬ ጣቶቸ መወገድ እንዳለባቸው ነገሩኝ ያ ካልኾነ ግን ወደ ከፋ አደጋ እንደሚያመራ ተነገረኝ ነው ያሉት።
በወቅቱ በሐኪሞች ሃሳብ አልተስማማሁም ነበር ያሉት አቶ በላይነህ ጣቶቸን ማጣት በጣም ትልቅ ነገር ስለሆነብኝ እንቢ አልኩ፤ ነገር ግን ከተወሰኑ ቀናት በኋላ መፍቀዴ ግድ ኾነ ጣቶቸም ተወገዱ ብለውናል።
በጣት በሚቆጠሩ ቀናት ነገሮች ተቀይረው ነበር፤ የተቆረጡትን ጣቶቸን አልፎ ወደ ሌላ አካል ተዛምቷል ተብዬ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ጉልበቴ ከፍ ብሎ እንድቆረጥ ተደረገ ነው ያሉት።
በዕለቱ ነገሮች ከበዱብኝ ከመኖር መሞትን መርጨ ነበር ብለዋል። ጋንግሪኑ በፍጥነት በሰዓታት እና በቀናት ወደ ላይ እየወጣ ስለኾነ በሕይወት ለማትረፍ እንደገና ታፋዬ ላይ መቁረጥ ግድ ኾነ ብለዋል። በጥቅል ስቃዩ ከባድ እንደነበር አስታውሰዋል። ወቅቱን ጠብቆ ሕክምና አለመውሰድም ዋጋ እንደሚያስከፍል በተግባር አይቻለሁ ነው ያሉት።
አሁን ላይ ያ ሁሉ አልፎ በአርቲፊሻል እግሮች እየተንቀሳቀስኩ ሕይወቴን እየመራሁ እገኛለሁ ብለዋል። ለቤተሰቦቻቸው ተስፋ ኾነው እንዳሉም ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ 22 ማዞሪያ የውስጥ ደዌ ስፔሻላይዝድ ክሊኒክ የጠቅላላ ሐኪም ዶክተር ሙላት ይመር ጋንግሪን በጣም አደገኛ የኾነ እና የቁስል ማመርቀዝን የሚያስከትል በሽታ ነው ብለዋል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ቁስለቱ የሚያጋጥመው በእግር እና እጅ ጣቶች ላይ ቢኾንም በማንኛውም የአካል ክፍል ላይ ሊከሰትም ይችላል ነው ያሉት፡፡
በተለያዩ አደጋዎች እና ሌሎች ምክንያቶች በአካላችን የተለያዩ ክፍሎች ላይ የደም ዝውውር ቢቋረጥ የተቋረጠበት የሰውነት ክፍል ጋንግሪን ሊፈጥር እንደሚችል ገልጸዋል።
ከምልክቶቹ ውስጥ በቁስሉም ላይ መጥፎ ጠረን ያለው ግራጫ ወይም ቡናማ ዓይነት ፈሳሽ ይወጣል ብለዋል፡፡ ቁስሉ አካባቢ ያለው ቆዳ ጠቆር ብሎ ውኃ ሊቋጥር እንደሚችልም ተናግረዋል፡፡ የቁስል ማመርቀዝ አደጋው ከተከሰተ ከ6 ሰዓት እስከ ሦስት ቀናት ባለው ጊዜ ውስጥ ሊጀምር እንደሚችል ገልጸዋል።
የጋንግሪን በሽታ በአጭር ጊዜ ውስጥ በሽታው እየከፋ እና ቁስሉም እየሰፋ የመሄድ ባሕሪም አለው ብለዋል፡፡ አስፈላጊው ሕክምና በፍጥነት ካልተሰጠ በጥቂት ቀናት ውስጥ ለሞት ይዳርጋል ነው ያሉት።
ጋንግሪን መጀመሪያ ከነበረበት ቦታ ሊስፋፋ የሚችል የጤና ችግር ስለኾነ ከፍተኛ ትኩረት ያስፈልገዋል ያሉት ዶክተር ሙላት ይመር በእግር ጣቶች መሐል፤ በሌላ የሰውነት ክፍል ላይ የሚፈጠርን አነስተኛ ቁስለት ችላ ማለት እንደማይገባም አሳስበዋል።





በሽታው አብዛኛውን ጊዜ የሚከሰተው በስኳር፣ በልብ፣ በደም ግፊት ሕሙማን ላይ በመኾኑ እነዚህ በሽታዎች ያሉባቸው ሰዎች የተለየ ክትትል ማድረግ አለባቸው ያሉት ዶክተሩ በተለይ የስኳር ሕመም ያለባቸው ሰዎች ቁስለቶችን ችላ ሳይሉ ተከታትለው ወዲያውኑ እንዲድን ማድረግ አለባቸው ብለዋል።
ሰዎች በጋንግሪን ሕመም ከተጠቁ በኋላ ግን የመጀመሪያ ሕክምናው ጋንግሪን የሞተ የአካል ክፍል በመኾኑ የተጠቃውን በድን አካል ማስወገድ ብቻ ነው መፍትሔ ይላሉ።
ነገር ግን ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ በዚህ ምርጫ ደስተኞች አይኾኑም ያ ኾነ ማለት ደግሞ ጋንግሪኑ ስር እየሰደደ ሌላውን ጤነኛ አካል መበከሉን ልብ ሊሉ ይገባል ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- ሰመሀል ፍስሐ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!