
ባሕር ዳር: ጥቅምት 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ቢሮ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አሥተዳደር ( ኢንሳ) ጋር በመተባበር 6ኛውን ሀገር አቀፍ የሳይበር ደኅንነት ወር አስመልክቶ የፓናል ውይይት እያካሄደ ነው።
በፓናል ውይይቱ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አሥተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሃሚድን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ “ኢትዮጵያውያን የጥንት ሥልጣኔ፣ በዘመን የደረጀ የሀገረ መንግሥት ግንባታ ያለን ነን” ነው ያሉት። “ነገር ግን ዓለም ከደረሰበት ምጡቅ የቴክኖሎጂ ምኅዳር ወደ ኋላ የቀረን ነን” ብለዋል።
ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ ተስተካካይ እና ተወዳዳሪ በማይኾን የቴክኖሎጂ እጥረት ውስጥ መቆየቷንም ገልጸዋል። “በኢኮኖሚ ወደ ኋላ መቅረታችን፣ ለፈጠራ የማይመች ይልቁንም ፈጠራን የሚኮንን ልምድ መኖር፣ ፈጠራን የማያበረታታ የትምህርት ሥርዓት ስለነበርን እና ሥልጣኔያችንን የሚመጥን የተመቻቸ ፖለቲካ ሥርዓት ስላልነበረን ከቴክኖሎጂ ርቀን ቆይትል” ነው ያሉት።
“በዚህም ምክንያት ከቴክኖሎጂ ከሚያስገኘው ትሩፋት ባይታወር ኾነን ቆይተል” ብለዋል። በዚህ ዘመን ልማት የሚተረጎመው በሰው ሃብት እና በቴክኖሎጂ ልማት መኾኑንም አንስተዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት አሁን ላይ በአዲሱ የሀገር በቀል ስትራቴጂ ከአምስቱ የኢኮኖሚ ምሰሶዎች መካከል የቴክኖሎጂ ልማት አንዱ አድርጎ እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
ሥራውን ገቢራዊ ለማድረግ የዲጂታል ስትራቴጂ ነድፎ እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል። ስትራቴጂውን የሚመራ እና የሚተገበር ተቋም እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። ይህን ለማረጋገጥ እየተሠራ ነው ብለዋል። የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አገልግሎትን ጨምሮ ሌሎች የቴክኖሎጂ ተቋማት ኢትዮጵያን በቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል።
አሁን ላይ ኢትዮጵያን በቴክኖሎጂ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎች እየተሠሩ ነው ብለዋል። በቴክኖሎጂ ተጠቃሚ መኾን ብቻ ሳይኾን አብዛኞቹ የሚተገበሩት በራስ አቅም በመኾናቸው ልዩ ያደርጋቸዋል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ የልማት ተግባራት አፈጻጸም የሚለካው በቴክኖሎጂ ልማት መኾኑንም ተናግረዋል። ቴክኖሎጂ አንድም የምርት ማሳደጊያ በሌላ በኩል ደግሞ የአገልግሎት ማሳለጫ ነው ብለዋል።
የአማራ ክልል የቴክኖሎጂ አስፈላጊነትን በመረዳት ለቴክኖሎጂ ልዩ ትኩረት እንዲሰጠው አድርጓል ነው ያሉት። በ25 ዓመታት ዕቅዱ ውስጥ ልዩ ትኩረት እንደተሰጠውም ተናግረዋል። ቴክኖሎጂውን የሚመራውን ተቋም ማሻሻል መቻሉንም ገልጸዋል።
በተሠራው ሥራ ተስፋ ሰጪ ጅማሮዎች መኖራቸውን ተናግረዋል። የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አሥተዳደር ላደረገው እና እያደረገው ላለው ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል።
“በዚህ ዘመን ልማት ማለት ሰብዓዊ ልማት እና ቴክኖሎጂ ልማት መኾኑን በውል እንረዳለን” ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ሌሎቹ የልማት ዘርፎች የዚህ ተከታዮች እና ቴክኖሎጂ የሚያሳልጣቸው ናቸው ብለዋል። የምርታማነት ደረጃ የሚጨምረው ቴክኖሎጂን መጠቀም እንደኾነም ተናግረዋል።
የቴክኖሎጂ ልማትን በሳይበር ደኅንነት መጠበቅ እንደሚገባም አስገንዝበዋል። የሳይበር ደኅንነት ለሀገር ትልቅ ፋይዳ እንዳለውም ተናግረዋል። የሳይበር ደኅንነት ወርን ማክበር የቴክኖሎጂ ንቃተ ሕሊናን ለመጨመር እንደሚያስችልም ገልጸዋል።
ቅንጡ ከተሞችም (ስማርት ሲቲን) ለመፍጠር ቴክኖሎጂን መጠቀም እንደሚገባ ተናግረዋል። ቅንጡ ከተሞችን ለመፍጠር ቴክኖሎጂ ኀይል ቀያሪ መኾኑንም ገልጸዋል። “የቴክኖሎጂ አጠቃቀማችን እያሻሻልን ወደፊት መራዳመድ መቻል አለብን” ብለዋል።
የአማራ ክልል መሪዎች ለቴክኖሎጂ ልማት ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩም አሳስበዋል። ቴክኖሎጂን በአግባቡ መጠቀም ካልተቻለ በደቂቃዎች ውስጥ የማውደም አደጋ እንደሚያመጣም ተናግረዋል። ጉዳት እንዳይደርስ የሳይበር ደኅንነትን ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን