
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የ2018 የሥራ ዘመን የዳኝነት አገልግሎትን በይፋ አስጀምሯል።
ጥቅምት 3/2018 ዓ.ም ፍርድ ቤቶች ከዕረፍት የተመለሱ ሲኾን የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የዳኝነት ችሎትም መጀመሩን ለአሚኮ ተናግረዋል።
በአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ የሥራ ሂደት አስተባባሪ ዳኛ ሃብታሙ አደራ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ጨምሮ ለእረፍት ተዘግተው የነበሩ የተዋረድ ፍርድ ቤቶች መከፈታቸውን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የለውጥ ሥራዎችን ማከናወኑን ጠቅሰው ለበለጠ የአገልጋይነት ስሜት፣ ለምቹ የሥራ ከባቢ እና ለግልጽ ችሎት ኹኔታዎችን ማመቻቸቱን አንስተዋል።
ዲጂታላይዜሽንን በመተግበርም ባለጉዳዮች ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ (ባሕር ዳር) መምጣት ሳይጠበቅባቸው ባሉበት ኾነው የዳኝነት አገልግሎት የሚያገኙበት እና ተደራሽነትን የሚያሻሽል አሠራር መጀመሩንም ነው ዳኛ ሃብታሙ የገለጹት።
የአገልጋይነት ስሜትን ለማሳደግ መሠራቱ እና የችሎት አዳራሾች መመቻቸት የቀጠሮ ብዛትን በመቅረፍ ጉዳዮች በፍጥነት እንዲጠናቀቁ እንደሚያስችልም ገልጸዋል።
የሥነ ምግባር፣ የአመለካከት፣ የዳኝነት ክህሎት እና የአገልጋይነት ስሜትን የሚያሳድጉ ሥራዎች መሠራታቸውን ያነሱት ዳኛ ሃብታሙ ይህም የዳኝነት አገልግሎቱን እንደሚያሻሽለው ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!