
አዲስ አበባ፡ ጥቅምት 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) 18ኛው ብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተከብሯል።
በዓሉ “ሠንደቅ ዓላማችን ለኢትዮጵያ ታላቅ የከፍታ ዘመን ብሥራት፣ ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችን እና ለኢትዮጵያ ሕዳሴ” በሚል መሪ መልዕክት ነው የተከበረው።
በበዓሉ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ሠንደቅ ዓላማችን የታሪኮቻችን፣ የአንድነታችን እና የሉዓላዊነታችን መገለጫ ነው ብለዋል።
“ሠንደቅ ዓላማው ታሪካችንን የምናወሳበት፤ የዛሬ ተግባራችን የምናጸናበት እና ነጋችንን የምንገነባበት ነው” ብለዋል በመልዕክታቸው።
ቀኑ የታላቁ የሕዳሴ ግድብ በተጠናቀቀበት እና ፕሮጀክቶችን ሠርተን ማጠናቀቅ እንደምንችል ባሳየንበት ማግስት መከበሩ ልዩ ያደርገዋል ነው ያሉት።
በቀጣይም የዜጎች የምግብ ሉዓላዊነት የሚረጋገጥበት ትልልቅ ፕሮጀክቶች በጋራ የሚሠሩበት እንደሚኾንም አመላክተዋል።
በበዓሉ በሠንደቅ ዓላማ ፊት ቃለ መሐላ የመፈጸም መርሐ ግብር ተካሂዷል።
ዘጋቢ፦ ኤልሳ ጉዑሽ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!