
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት 18ኛውን የሠንደቅ ዓላማ ቀንን “ሠንደቅ ዓላማችን ለኢትዮጵያ ታላቅ የከፍታ ዘመን ብሥራት፣ ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችን እና ለኢትዮጵያ ሕዳሴ” በሚል መሪ መልዕክት አክብሯል።
በበዓሉ የፌዴራል ፖሊስ አባላት፣ የክልሉ ፖሊስ ማርሽ ባንድ እና የአድማ መከላከል ፖሊስ አባላት የተለያዩ የሰልፍ ትርዒቶችን አሳይተዋል።
በበዓሉ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) የሠንደቅ ዓላማ መከበር ዋናው ዓላማው የሀገርን ሕልም እና ራዕይ ለዜጎች ለማስገንዘብ ነው ብለዋል።
ዜጎች የሀገራቸውን ሕልም ለማሳካት እና በሠንደቃቸው ቀለማት ሰይመው በማስታወስ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉም ያግዛል ነው ያሉት።
ሠንደቅ ዓላማ በሀገረ መንግሥት ግንባታ የሚኖረውን ኅብረ ብሔራዊነት እና አንድነት ለማሳየት ብቻ ሳይኾን የሀገርን ራዕይ በአንድ ምልክት ጠቅልሎ የሚያስረዳም ነው ብለዋል።
የሠንደቅ ዓላማ ቀን ሲከበር ስለአከባበሩ እና ለምን እንደሚከበር ሁሉም ዜጎች በውል ሊገነዘቡት እንደሚገባም ተናግረዋል።
የዚህ ዓመት የሠንደቅ ዓላማ ቀን ልዩ የሚያደርገው ለሀገራዊ ማንሠራራት እና ከፍታ ምልክት የኾኑ ትላልቅ ፕሮጀክቶች በተመረቁ ማግሥት እና መጭውን ሀገራዊ ልዕልና የሚያበስሩ ልማቶችም በተጀመሩበት ወቅት መከበሩ ነው ብለዋል።
ሠንደቅ ዓላማ ሲታሰብ በደም እና በአጥንት የሀገር ሉዓላዊነት እና ክብር መጠበቁ ይታወስበታል ነው ያሉት።
የደም እና የአጥንት መስዋዕትነት ከሁሉም ዜጎች የሚጠበቅ ቢኾንም በተለይም ደግሞ ከመለዮ ለባሾች የሚጠበቀው መስዋዕትነት ከፍ ብሎ ይታያል ብለዋል።
“የሠደቅ ዓላማን መውደድ ሀገርን ከባዕዳ እና ከባንዳ መጠበቅም ነው” ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ
ሠንደቅ ዓላማውን የሚወድ ሁሉ ሀገሩን ከባዕዳን ተልኮ መጠበቅ እና መከላከል እንደሚገባው አሳስበዋል።
ሠንደቅ ዓላማን እንደሚያከብሩ ዘወትር መናገር እና ቀለሙን ለብሶ መታየት ብቻ የሀገር ፍቅርን እንደማይገልጽም አመላክተዋል።
ባዕዳን ሀገርን ለማተራመስ ሲሞክሩ መተባበር እና አብሮ መውጋት በትክክለኛ ስሙ “ባንዳነት” ነው ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ እንደዚህ አይነት ዓላማ ያላቸው ሁሉ ቆም ብለው እንዲያስቡ መልዕክት አስተላልፈዋል።
“ሠንደቅ ዓላማችን ለያዛቸው መልዕክቶች እና መርሆዎች ተገዥ በመኾን ልዩነቶችን በሰላም ፍቱ እንጅ ለሀገር እና ለሕዝብ የማይበጁ የባዕዳንን ተልዕኮዎች አትሸከሙ” ነው ያሉት።
የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አማረ ሰጤ ሠንደቅ ዓላማችን ለኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን እና አብሮነታችን ማሳያ ኾኖ ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፍ ምልዕክታችን ነው ብለዋል። የነጻነት እና የሉዓላዊነት መገለጫ መኾኑንም ገልጸዋል።
ሠንደቅ ዓላማ የአንድ ሀገር መለያ ምልክት፣ የማንነት ክብር፣ ከፍ ብሎ መታያ እና መገለጫ ነው ብለዋል። ሁሉም ዜጎች ክብር ሊሰጡት እና ሊጠብቁት የሚገባ መኾኑን አስገንዝበዋል።
የሠንደቅ ዓላማ ቀን በክልሉ ሲከበር የፌዴራል እና የክልሉ የጸጥታ አካላት ለአማራ ክልል ሰላም መኾን ስለከፈሉት ዋጋ ዕውቅና እና ክብር የሚሰጥበት መኾኑንም ምክትል አፈ ጉባኤው ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!