
ባሕር ዳር: ጥቅምት 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ለ18ኛ ጊዜ የሠንደቅ ዓላማ ቀን ዛሬ ጥቅምት 3 ቀን 2018 ዓ.ም እየተከበረ ነው።
ደሙን ያፈሰሰ ልቡ እየነደደ
በአርበኝነት ታጥቆ ጠላት ያስወገደ
ንጉሡን ሀገሩን ክብሩን የወደደ
ነጻነቱን ይዞ መልካም ተራመደ።
ገናናው ክብራችን ሠንደቅ ዓላማችን
ያኮራሻል አርበኝነታችን።
ይህ መዝሙር በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመን ተማሪዎች ሠንደቅ ዓላማን ሲያወጡ የሚዘምሩት መዝሙር ነበር ይላሉ የአማራ ክልል የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ሊቀ መንበር ዳኝነት አያሌው።
በአማራ ክልል የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ሊቀ መንበር ዳኝነት አያሌው ሠንደቅ ዓላማ ብሔራዊ ኩራት፣ የሀገር ሉዓላዊነት እና የእኩልነት መገለጫ መኾኑን ገልጸዋል።
በጣሊያን ወረራ ጊዜ ኢትዮጵያውያን በአንድነት በሠንደቅ ዓላማቸው ሥር ኾነው ተዋግተው ድል ማድረጋቸውንም አስታውሰዋል።
ከአንደኛው የዓለም ጦርነት መጠናቀቅ በኋላም ሌግ ኦፍ ኔሽን ሲመሠረት ከአፍሪካ ነጻነት ያላት ኢትዮጵያ ብቻ ስለነበረች ሠንደቅ ዓላማዋም በዓለም መድረክ መውለብለቧን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያን የነጻነት ተምሳሌት በመከተልም የአፍሪካ ሀገራት የሠንደቅ ዓላማችን ቀለማት እንደተጠቀሙበት እና የካሪቢያን ሀገራትም ሠንደቅ ዓላማችን ወድደው አክብረው እንደሚይዙት ጠቅሰዋል።
የአሁኑ ትውልድም ይህንን ጀግኖች ቆስለው እና ተሰውተው፣ በክብር ያቆዩዋትን፣ የክብር እና የሉዓላዊነት መገለጫ የኾነችውን ሠንደቅ ዓላማ አክብሮ መያዝ እንዳለበት መክረዋል።በተሳሳተ ትርክት ታሪክ እንዳይዛባ መጠንቀቅ እንደሚገባም መክረዋል።
ሠንደቅ ዓላማ ሲወጣ እና ሲወርድ እግረኛም ቆሞ፣ ፈረሰኛም ከፈረሱ ላይ ወርዶ፣ ክንንብም ወርዶ በክብር በመቆም ይከበር እንደነበር አስታውሰዋል።
መንግሥት ታሪክን የማቆየት፣ ምሁራን ደግሞ እውነተኛ ታሪክን የማስተማር ኀላፊነት እና ትውልዱ ደግሞ ታሪክን አውቆ የመጠበቅ ኀላፈነት እንዳለባቸው ነው የገለጹት።
ተጠማጅ አርበኛ በሀገር መውደድ ቀንበር
ገዳይ ድል አድራጊ ደመላሽ ወታደር
አንቺን እያሰበ ይጓዛል ሲፎክር
ሠንደቅ ዓላማችን የነጻነት ሀገር።
ገናናው ክብራችን ሠንደቅ ዓላማችን
ያኮራሻል አርበኝነታችን።
ይህ ደግሞ እነ አርበኛ ዳኝነት በትምህርት ቤት ጊዜያቸው ሠንደቅ ዓላማ ሲያወርዱ የሚዘምሩት መዝሙር ነበር።
በአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የኮሙዩኒኬሽን እና የሕዝብ ግንኙነት ዋና መምሪያ ኀላፊ ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ወንዴ ሠንደቅ ዓላማ ሲነሳ ከሚታወሱት መካከል አንዱ ፖሊስ መኾኑን ገልጸዋል።
ፖሊስ መሠረታዊ ሥልጠናውን አጠናቅቆ ሲመረቅ ቃለ መሐላ የሚፈጽመው በሠንደቅ ዓላማ ፊት መኾኑንም ጠቅሰዋል።
ሠንደቅ ዓላማ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት፣ የነጻነት፣ የጀግንነት እና የአንድነት መገለጫ ነው። ይህንን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ነው ፖሊስ ሥራውን ሲጀምር ስለሠንደቅ ዓላማ እያሰበ የሚኾነው ብለዋል።
ሠንደቅ ዓላማችን የሰላም እና የነጻነት ምልክት ነው፤ ለፖሊስም ልዩ ትርጉም አለው ያሉት ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ፖሊስ ለሕዝብ ክብር እና ለሀገር ሉዓላዊነት በግንባር ቀደምነት ሲሰለፍ ሠንደቅ ዓላማን አንግቦ መኾኑንም ጠቅሰዋል።
ሠንደቅ ዓላማ ለፖሊስ ከፍ ያለ ስሜት፣ ትርጉም እና ክብር ያለው ነው። ፖሊስ ወንጀልን በመከላከል የሕዝብ ሰላምን ከመጠበቅ እና ወንጀለኛን ለሕግ በማቅረብ ፍትሕን ከማስፈን ጎን ለጎን ኅብረተሰብን በሚያገለግልባቸው የስፖርት እና የኪነ ጥበብ ዘርፍም ለሠንደቅ ዓላማ ክብር እና ከፍታ አስተዋጽኦ እያበረከተ መኾኑን ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያም የሠንደቅ ዓላማ ማውጣት እና ማውረድ ሥነ ሥርዓትን የሪፎርሙ አካል አድርጎ እየሠራ ነው። በመኾኑም በዓመት አንድ ቀን በዓል ማክበር ብቻ ሳይኾን በየዕለቱ ለሠንደቅ ዓላማ የሚገባውን ክብር እየተከወነ ነው። በዚህም የአካባቢው ማኅበረሰብ እና በየደረጃው የሚገኙ የፖሊስ አባላት ትምህርት የሚወስዱበት ነው ብለዋል። በዞን እና ወረዳዎችም የሠንደቅ ዓላማ ክብር እንዲጠናከር እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
የሠንደቅ ዓላማ ቀንን ስናከብር ስለ ሰላም በመወያየት፣ ሁሉም የሰላም ጉዳይ የኔ ጉዳይ ነው በማለት ስለ ሰላም በመነጋገር ሊኾን ይገባል ነው ያሉት።
የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባዔ አማረ ሰጤ የሠንደቅ ዓላማ በዓልን የማክበር ዓላማው ሠንደቅ ዓላማ ለብሔራዊ አንድነታችን እና ሉዓላዊነታችን ያለውን መገለጫነት ለማስገንዘብ ነው ይላሉ።
በዓሉ ቀደምት ከአርበኞች ጀምሮ እስከ አሁኑ የመከላከያ ሠራዊት ድረስ በሠንደቅ ዓላማ ሥር ለሀገር ሉዓላዊነት የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ እና የሚከፍሉትን መስዋዕትነትም በማሰብ ክብር የሚሰጥበት መኾኑን ተናግረዋል።
የሠንደቅ ዓላማ ቀንን በዓመት አንድ ቀን ከማክበርም በላይ በየዕለቱ በአዋጅ በተደነገገው መሠረት እንዲፈጸም ለማድረግ ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል። አንዳንድ ዞኖች እና ተቋማትም የሠንደቅ ዓላማ ክብርን የጠበቀ ሥራ መጀመራቸውን እና ያንን አጠናከሮ ለማስፋት እንደሚሠራ ነው ምክትል አፈ ጉባኤው የገለጹት።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን