
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት የሰንደቅ ዓላማ ቀንን አስመልክቶ መልዕክት ስተላልፏል።
በመልዕክቱም ስኬቶቻችን የሰንደቃችን ከፍታ የሚጨምሩ ናቸው ብሏል።
ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት የለውጥ ዓመታት እመርታዊ ስኬቶችን እያስመዘገበች የሚመጥናትን ከፍታ እየያዘች ትገኛለች፡፡ ለዘመናት የቁጭት እና እንጉርጉሮ ትርክት ምንጭ የነበረዉን ዓባይን ገርታ የኃይል እና ብርሃን ምንጭ አድርጋለች ነው ያለው።
በንጋት ኃይቅ በምግብ ሉዓላዊነቷ ላይ ጉልህ ሚና የሚጫወት የዓሣ ምርት ማግኘት ችላለች፤ ዐዲስ የቱሪዝም መዳረሻ ደሴቶችንና ከተሞችን ፈጥራለች፡፡ የዓባይን የቁጭት ትርክት ወደ ድል እና አሸናፊነት ብስራት ቀይራለች፡፡ ተጨማሪ የኃይል ምንጮችን ከውኃ እስከ እንፋሎት፣ ከፀሐይ ብርሃን እስከ
ኑውክሊየር ኃይል እና ነፋስ በመገንባት ላይ ናት፡፡ እነዚህ ሁሉ የሰንደቋን ከፍታ እና ተምሳሌትነት የሚያጎሉ ናቸው ብሏል።
ኢትዮጵያ ከገጸ ምድር ባሸገር በከርሰ ምድር ያሉ ሀብቶቿን ወደመጠቀም ተሸጋግራለች፡፡ በተፈጥሮ ጋዝ ማውጣት የታየዉን ስኬት ለማላቅ፣ በነዳጅ ዘይትም ለመድገም ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ጀምራለች፡፡ የግብርና ዘርፉን ውጤታማነት ለማሳደግ የአፈር ማዳበሪያ በራሷ ለማምረት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ደርሳለች።
የሕዝቧን የአኗኗር ዘይቤ ለመቀየር ከቢሮ እስከ ግቢ በሚል ጀምራ፣ ከከተማ እስከ ገጠር ወደሚል ተሸጋግራለች፡፡ በአዲስ አበባ የተጀመረዉ የከተሞችን ገጽታ የመቀየር ንቅናቄ ዘመናዊነትን፣ የስማርት ሲቲ ጽንሰ ሐሳብን እና ሰውን ከተፈጥሮ የማስማማት ልምምድን ያስተዋወቀ ነው፡፡ ይህም የዲፕሎማሲ
ማእከል የሆነችውን መዲናችንን በዓለማቀፍ ደረጃ ያላትን ገጽታ የሚያጎላ፣ የሰንደቃችንን ከፍታ የሚጨምር ኾኗል ብሏል።
ከተሞቻችንን የማዘመኑን ጅማሮ ወንዞቻችን በማከም የተፋሰሶችን ደኅንነት የሚያረጋግጥ ኾኗል፡፡ ከእንጦጦ ጀምሮ እየተሠራ ያለዉ የወንዞች ዳርቻ ልማት የአዋሽ ተፋሰስን ሥነ ምኅዳር ጭምር
የሚያክም ለአካባቢ ጥበቃ አብነት ነው፡፡ የገጠር አኗኗር ዘይቤያችንን በማዘመን ኢትዮጵያን በበጎ የምትመሰል ሀገር የማድረግ ጥረታችንም ፍሬው እየታየ ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ የሰንደቃችንን በኩራት መውለብለብ የሚያጎሉ የትጋታችን ውጤቶች ናቸው ነው ያለው።
ዛሬ የምናከብረው የሰንደቅ ዓላማ ቀን በነፃነት ቀን የተገኘ አይደለም፤ ነፃ ሆኖ ለሌሎች ነፃነት ከፍ ብሎ ሲውለበለብ የታየ የነፃነት ምልክት እንጅ፡፡ ነፃነቱን ለማስከበር ግን ቀደምቶቻችን ደም፣ ሥጋ እና ዐጥንት ገብረዋል፡፡ ኢትዮጵያን የዓለም የነፃነት ቀንዲል አድርገዉ አስረክበውናል፡፡
ዛሬም እንደትናንቱ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በደም እና በዐጥንት ለማስከበር የቆረጡ ጀግኖች አሉን፡፡ በምድር፣ በአየር፣ በባሕር እና በሳይበር የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በማስከበር ሰንደቋ የነፃነት ተምሳትነቱ እንዲቀጥል የሚተጉ ጀግኖቻችን አሉ፡፡ የሰንደቅ ዓላማ ቀንን የምናከብረዉ በሁሉም ግንባር፣ በሁሉም ዓውድ ስለኢትዮጵያ ዋጋ የሚከፍሉ ጀግኖቻችን በማመስገን፣ ሰንደቃችንም በክብር ከፍ አድርገን በማውለብለብ፣ ለላቀ ከፍታዉ እንደምንተጋ
ቃል በመግባት ነው ብሏል።
የተጀመሩ ትልልቅ የሰንደቅ ዓላማ ፕሮጀክቶች ለማሳካት ደግሞ ያለስስት በጋራ መጣር፣ የኢትዮጵያን ብልጽግና እውን ለማድረግ ማናቸውንም ዋጋ መክፈል ከዜጎች ይጠበቃል ነው ያለው በመልዕክቱ።
እንኳን ለሰንደቅ ዓላማ ቀን አደረሳችሁ!
የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት
ጥቅምት 3/2018 ዓ/ም
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!