
ባሕር ዳር: መስከረም 28/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በክረምት በጎ ፈቃድ መርሐ ግብር በሃላባ እና ከምባታ ዞኖች የተገነቡ ሞዴል የገጠር መንደሮችን አስረክበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ዛሬ በክረምት በጎፈቃድ መርሐ ግብር በሃላባ እና ከምባታ ዞኖች የተገነቡ ሞዴል የገጠር መንደሮችን አስረክበናል ብለዋል።
እነኚህ መንደሮች የአርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮችን ሕይወት ለማሻሻል የምናደርገው ጥረት ተስፋ ሰጪ ጅማሮ ናቸው። ቤቶቹ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ የተገጠመላቸው፣ ለማብሰል ደግሞ ከእንስሳት እዳሪ ባዮጋዝ የሚጠቀሙ፣ የተለየ ሳሎን፣ መጸዳጃ እና ሰርቪስ ቤቶች የተሟላላቸው ናቸው ነው ያሉት።
ንጽሕናን በሚያረጋግጥ እና የአኗኗር ደረጃን ከፍ በሚያደርግ አኳኋን የተለየ የእንስሳት በረት ተሰርቶላቸዋል። እነዚህ የገጠር ኮሪደር ልማት መንደሮች የገጠሩን አኗኗር የማሳደግ ሕልማችን አካል በመሆን ተስፋፍተው የሚሠሩ ይሆናል ብለዋል።
ባለፉት ሰባት ዓመታት የክረምት በጎ ፈቃድ በከተሞች ለሚኖሩ ለችግር የተጋለጡ ወገኖች መኖሪያ ቤቶችን ስናቀርብ ቆይተናል። አሁን ደግሞ በገጠር ኮሪደር ልማት የሥራውን እመርታ ወደገጠር አስፋፍተናል። ግለሰቦች፣ ድርጅቶች እና የዲያስፖራው ማኅበረሰብ እነኚህን ሥራዎች እንዲደግፉ እና እንዲሳተፉ አበረታታለሁ።
ባለፈው ጉብኝቴ ወቅት ያቀረብኩላቸውን የቤት ሥራ በመወጣት በአጭር ጊዜ ውስጥ በራስ አቅም የሀምበሪቾ ተራራ ደረጃንም በእጥፍ ሠርተው ላጠናቀቁት መሪዎች ያለኝን ምስጋና አቀርባለሁ። ወደፊትም የየአካባቢ መሪዎች ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተሠሩትን ሞዴል መንደሮች በመጪው ዓመት በየዞኑ ወደ100 ቤቶች እንዲያሳድጉ አሳስባለሁ ብለዋል በመልዕክታቸው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!