
አዲስ አበባ፡ መስከረም 28/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ዛሬ ያስጀመሩት ማዕከል በተሟላ ኹኔታ ፈጣን እና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ነው ብለዋል።
ማዕከሉ ከብልሹ አሠራር የፀዳ እና ለሚነሱ ቅሬታዎች ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚያስችል መኾኑንም ገልጸዋል።
በከተማዋ የሚስተዋለውን የቢሮክራሲ ችግር ለመቅረፍ በአራዳ ክፍለ ከተማ የተጀመረው የመሶብ ዲጂታል የአንድ ማዕከል አገልግሎት በቦሌ ክፍለ ከተማም ልህቀትን መተግበር እንዲያስችል ተደርጎ በዘመናዊ መንገድ መገንባቱን ከንቲባዋ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ.ር) ዛሬ የተመረቀው ማዕከል እስከዛሬ በከተማዋ ከተገነቡት የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫዎች በጥራት እና በቴክኖሎጂ የላቀ መኾኑን ገልጸዋል።
ተገልጋዮች ወደ ማዕከሉ ሲመጡም በውስጡ የ96 ተቋማትን አገልግሎት በአንድ እንዲያገኙ የሚያስችል መኾኑን ጠቁመዋል።
በከተማ አሥተዳደሩ የተጀመረው የመሶብ ዲጂታል አንድ ማዕከል አገልግሎት በክልሎች እንዲስፋፋ ይሠራልም ብለዋል።
የከተማ አሥተዳደሩ ፐብሊክ ሰርሺስ እና የሰው ሃብት አሥተዳደር ኀላፊ ጀማል ጀንበሩ (ደ.ር) የመንግሥት ተቋማት ዋነኛ ግብ ከሕዝብ እና ከመንግሥት የተሰጣቸውን ተልዕኮ በብቃት መፈፀም እንደኾነም ጠቁመዋል።
የዜጎችን ምርታማነት እና የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትን ለማላቅ የተለያዩ የፌዴራል እና የከተማ አሥተዳደሩን አገልግሎቶች በውስጡ ይዞ የዜጎችን ወጭ እና እንግልት በመቀነስ ትልቅ ፋይዳ ያለው ነው ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ቤተልሄም ሰለሞን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!