
ባሕር ዳር: መስከረም 28/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በእለት ከእለት የመዝገብ ሥራዎች ከበርካታ ባለጉዳዮች ጋር የሚገናኙት የክልሉ ዳኞች ፣ከባለጉዳዮች እና ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር እንዲሁም በሌሎች የግል ህይወታቸው በሚኖራቸው መስተጋብር ፣ መልካም ግንኙነትን ማዳበር እንዲችሉ የሚያግዛቸውን መሠረታዊ የኮሙዩኒኬሽን ክህሎት ስልጠና ወስደዋል።
ስልጠናውን የሰጡት የአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት እና የኮሙዩኒኬሽን መምህሩ ጌታቸው ድንቁ (ዶ.ር) ሲሆኑ፣ በኮሙዩኒኬሽን ምንነት፣ አይነቶች፣ ኮምዩኒኬሽን በቀን ተቀን የዳኞች ህይወት ውስጥ ያለውን አስተዋጽኦ፣ ውጤታማ የኮሙዩኒኬሽን ሰዎች በሥራ እና በግል ህይወታቸው ያላቸውን መልካም አጋጣሚ ፣ አለም ላይ በኮሙዩኒኬሽን ክህሎታቸው ተጽእኖ መፍጠር የቻሉ የታዋቂ ሰዎችን ልምድ እና ስኬት እያነሱ አስረድተዋል።
ኮምዩኒኬሽን ትብብርን ይፈጥራል ፣ ትብብር ደግሞ የጋራ ርዕይ ያለውና ዓላማውን ለማሳካት በላቀ ቁርጠኝነት የሚነሳ ፈጻሚ ለማፍራት ትልቅ ድርሻ እንዳለው በገለጻቸው ያስረዱት ዶክተር ጌታቸው፣ ስለ ተቋማዊ የኮሙዩኒኬሽን ስትራቴጂ፣ የኮምዩኒኬሽን ስትራቴጂ የአንድን ተቋም ርዕይ ለማሳካት ስለሚኖረው አስተዋጽኦ እና ዳኞችን በሥራ እና በግል ውጤታማ ማድረግ ስለሚችሉ ሌሎች የኮሙዩኒኬሽን ክህሎቶች ስልጠናዎችን ሰጠዋል።
ከዶክተር ጌታቸው ስልጠና በመቀጠል፣ የአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች የኮምዩኒኬሽን ስትራቴጂ ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበታል።
በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የኮሙዩኒኬሽን ምክትል ዳይሬክተር አቶ ጌትነት አላምር የቀረበው የክልሉ ፍርድ ቤቶች የኮምዩኒኬሽን ስትራቴጂ፣ የስትራቴጂውን ምንነት፣ አስፈላጊነት፣ አላማና ግቦች፣ ተግባራት፣ የማስፈጸሚያ ስልቶችና የውጤት መለኪያዎች በዝርዝር የያዘ ነው።
የኮምዩኒኬሽን ስትራቴጂው፣ ፈጣን፣ ወጥነት፣ ተከታታይነት እና ስልታዊ የኮምዩኒኬሽን ስራዎችን በመሥራት የክልሉ ፍርድ ቤቶች በማኅበረሰቡ ዘንድ ያላቸውን ተቀባይነት ማሳደግ፣ ግልጽ፣ ታማኝ፣ ተገማች፣ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ባለቤት እና ተምሳሌት የሆኑ ፍርድ ቤቶች በክልሉ ውስጥ እንዲኖሩ ለማድረግ በሚሰራው ሥራ የኅብረተሰቡን ተሳትፎ ለማጎልበት መዘጋጀቱ በገለጻው ተብራርቷል።
ስትራቴጂው የተቀመጠለትን ግብ እንዲያሳካ የፈጻሚ አካላት ሀላፊነት በዝርዝር ተቀምጧል።
በቀረበው ስትራቴጂ ላይ ውይይቶች የተካሄዱ ሲሆን ፣ ተሳታፊዎች ሀሳብ እና እና አስተያየታቸውን ሰጠውበታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!