
ባሕር ዳር: መስከረም 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ የትምህርት ቁሳቁስ ደጋፍ አድርጓል።
በድጋፍ ርክክቡ ላይ የተገኙት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) በክረምት ወራት” አንድ ደርዘን ደብተር ለአንድ ተማሪ” በሚል ንቅናቄ በተሠራ ተግባር 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ደብተር እና የተለያየ የመማሪያ ቁሳቁስ መሠብሠብ ተችሏል ብለዋል።
ሌሎች ድርጅቾችም አቅም ለሌላቸው ተማሪዎች የቁሳቁስ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል። ኮሚሽኑ ላደረገው ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዳጋቶ ኩምቤ ኮሚሽኑ በደም ልገሳ፣ በገጠር ኮሪደር ሥራ እና በትምህርት የግብዓት ድጋፍ ላይ እየተሳተፈ መኾኑን ገልጸዋል።
በዛሬው ዕለትም 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር የሚገመት ደብተር፣ እስክብሪቶ፣ እርሳስ እና የመሳሰሉ ቁሳቁሶችን ድጋፍ አድርጓል ነው ያሉት። በቀጣይም ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ ሀገሪቱ የጀመረችውን ልማት ለማፋጠን የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ መኾኑንም ገልጸዋል።
በ2017 በጀት ዓመት 4 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መሳብ መቻሉን አንስተዋል። ከ500 በላይ አዳዲስ ባለሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ ገብተው በተለያዩ ዘርፎች እየተሳተፉ ይገኛሉ ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- ዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!