
ባሕር ዳር፡ መስከረም 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ለሕዝብ የታመነ እና ለሕግ የቀረበ አሥተዳደር ብልጽግናን ለማረጋገጥ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ናግረዋል።
ይህም ውጤታማ እንዲኾን የአሥተዳደር ማዕቀፎችን በማሻሻል፣ የተቋማትን ቅንጅት በማጠናከር ተቋማት ውጤታማ እንዲኾኑ እየተሠራ እንደሚገኝም ነው ያስገነዘቡት።
መልካም አሥተዳደር የዘመናዊ ፖለቲካ የማዕዘን ድንጋይ ስለመኾኑም ነው የጠቆሙት። የሕዝብ ርካታን ለማምጣትም በ2025 የዕድገት ሽግግር ዕቅድ አመርቂ ውጤት መገኘቱንም አብራርተዋል።
በቀጣይም በዲጅታል አሠራል የተገኘውን ውጤት ይበልጥ ለማሻሻል እንደሚሠራም ፕሬዘዳንት ታዬ ተናግረዋል።
የመንግሥት ተቋማት የብዝኀነት ማዕከል እንዲኾኑ እንደሚሠራም ጠቁመዋል። ኅብረተሰቡ ሳይንገላታ አገልግሎት በቅልጥፍና የሚያገኝበት አሠራር የኾነውን የአንድ ሞሰብ አገልግሎት አጠናክሮ ለማስቀጠል ይሠራልም ነው ያሉት።
የመረጃ ትንተናን በማዘመን ሉዓላዊ አቅምን ለማሳደግ እንደሚሠራም አስገንዝበዋል። መንግሥት የዜጎችን ደኅንነት ለማስጠበቅ በ2018 ዓ.ም በትጋት እንደሚሠራም ነው ያብራሩት።
መንግሥት የዜጎችን ደኅንነት ለማስጠበቅም የፍትሕ ተቋማትን የማዘመን ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝም ነው ያብራሩት። የተሻሻሉ የወንጀለኛ መቅጫ እና የፍትሐ ብሔር ሕጉችም በቴክኖሎጂ እንዲታገዙ መሥራት መቻሉንም ነው ያስረዱት። የፍትሕ ተቋማትን በዲጂታላይዜሽን አሠራር ለማዘመን እየተሠራ እንደኾነም ነው የጠቆሙት።
ባሕላዊ የፍትሕ ሥርዓቶችም ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የማጠናከር ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል። በተያዘው ዓመት ድህነት ከሚፈጥረው እንግልት በመሻገር ልማትን የማረጋገጥ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን