
ባሕር ዳር፡ መስከረም 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የጋራ መክፈቻ ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል።
ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ የፌዴራል መንግሥቱን ዓመታዊ ዕቅድ አቅርበዋል።
መንግሥት በኮሪደር ልማት እና በተቀናጀ የመሠረተ ልማት ማስፋፊያ በርካታ ሥራዎችን አከናውኗል ብለዋል። በቀጣይነትም የከተማ ልማት ሥራ የድህነት ቅነሳን የሚያግዝ እና የተሻለ ገቢን በሚፈጥር መልኩ እንደሚከናወን ተናግረዋል።
የይዞታ ማረጋገጫ ሥርዓትን በማጎልበት የመሬት አቅርቦትን በማሳደግ የመሬት ይዞታ መብት እንዲረጋገጥ በትኩረት እንደሚሠራም ገልጸዋል።
በመንግሥት እና በግሉ ዘርፍ የጋራ ትብብር የቤት አቅርቦት ችግር በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቃለል ይደረጋል ብለዋል። በገጠሪቱ ኢትዮጵያም የመኖሪያ ቤት ደረጃ እንዲሻሻል እንደሚሠራም ተናግረዋል። የንጹሕ መጠጥ ውኃ፣ የመብራት፣ የትራንስፖርት ተደራሽነትን ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሠራም ገልጸዋል።
የቱሪዝም መዳረሻዎችን የማልማት እና የመሠረተ ልማት የማሻሻል ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉምም አንስተዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት ውብ ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚያስችሉ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎች እንደሚስፋፉ ገልጸዋል። ነባሮቹ የቱሪዝም መዳረሻዎችም ለጎብኝዎች ምቹ እንዲኾኑ ይደረጋልም ነው ያሉት።
የሕዝቡን ጥቅም የሚያስጠብቁ፣ የማኅበረሰብ ቱሪዝም ፕሮጀክቶችን በመተግበር የነዋሪውን ወግ እና ታሪክ የሚያሳዩ የባሕል ማዕከላትን አጣምሮ በመገንባት ለጎብኝዎች እና ለነዋሪዎች ምቹ እንዲኾኑም ይደረጋል ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!