
ባሕር ዳር፡ መስከረም 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት የ2018 ዓ.ም የሥራ ዘመን የጋራ መክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ባቀረቡት የመክፈቻ ንግግር ላይ በተያዘው በጀት ዓመት መንግሥት ሰላምን በማይናወጥ አቋም ላይ ለማስቀመጥ እና አንድነትን ለማጠናከር የተቋማት ግንባታ ላይ መንግሥት አበክሮ እንደሚሠራ ተናግረዋል።
የብሔራዊ ደኅንነት ማስጠበቂያ የጸጥታ እና ደኅንነት ተቋማትም የሥርዓት ለውጥን የሚሻገሩ እና የሀገርን ቀጣይነት የሚያረጋግጡ ብርቱ ተቋማት እንዲኾኑ እንደሚሠራም አስገንዝበዋል።
በየአካባቢው የሚታዩ ግጭቶችን መንግሥት በኀይል የማረቅ አቅም ያለው ቢኾንም ዘላቂ ሰላም የሚመጣው በመነጋገር እና በውይይት መኾኑን መንግሥት እንደሚያምን አስረድተዋል።
ለዚህም የተለያዩ የዕርቅ ስልቶችን በመንደፍ አስተማማኝ ሰላምን ለማረጋገጥ መንግሥት እየሠራ እንዳለም ነው የጠቆሙት።
መንግሥት ዛሬ ላይ በኀይል የማረቅ አቅም እና ዘመናዊ አሠራር ያለው ቢኾንም ለነገው ቁርሾ ላለመተው ዘመናዊ አሠራር እና ስልትን በመከተል ሰላምን ለማረጋገጥ ከመቸውም ጊዜ በላይ እየሠራ እንደሚገኝም ነው ያብራሩት።
ይህም ዘላቂ የኾነ ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግሥት ለመመሥረት እንደሚያግዝ ነው የተናገሩት። በዚህ ሥራ ላይ የላቀ ሚና ላለው የሀገራዊ ምክክር ሕዝቡ እና ምሁራን አስፈላጊውን እገዛ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን