“ዜጋን ማዕከል ያደረገ ብሔራዊ ደኅንነትን የማረጋገጥ ጉዳይ ቀዳሚው ነው” ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ

3
ባሕር ዳር: መስከረም 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የጋራ መክፈቻ ሥነ ሥርዓት እየተካሄደ ነው።
ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ የፌዴራል መንግሥቱን ዓመታዊ ዕቅድ አቅርበዋል።
ዓለም በተለዋዋጭ ሁኔታ ውስጥ እንደምትገኝ በዕለቱ ገልጸዋል። አፍሪካም ኾነ ኢትዮጵያ ከዚህ ኡደት ውጭ ሊኾኑ አይችልም ያሉት ፕሬዝዳንቱ በዚህ ዓለም እውነታ ውስጥ ሀገራዊ ሰላምን እና ደኅንነትን ማስጠበቅ፣ እደገት እና ብልጽግናን ማረጋገጥ፣ በዓለም አቀፍ፣ አሕጉራዊ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ንቁ ተሳትፎ እና የሰላ ተጽዕኖ ማሳረፍ ይገባል ብለዋል።
“ዜጋን ማዕከል ያደረገ ብሔራዊ ደኅንነትን የማረጋገጥ ጉዳይ ቀዳሚው መኾኑን” ተናግረዋል። ብሔራዊ ደኅንነት የሀገርን ዳር ድንበር ማስከበር ብቻ ሳይኾን የዜጎችን ደኅንነት እና ክብርንም ማስጠበቅን ይጨምራል ብለዋል።
በማንኛውም ቦታ የሚገኙ ዜጎቻችን ደኅንነት እና ክብር የሀገራዊ ደኅንነት ጉዳያችን ነው ብለዋል። ሕገ ወጥ ፍልሰትን መቆጣጠር፣ ዜጎች መብታቸው ተጠብቆ እንዲንቀሳቀሱ እና የሥራ ዕድል ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥ ማድረግ፣ በሚኖሩበት እና በሚሠሩባቸው ሀገራት መብታቸው እንዲከበር ማድረግ ትኩረት የሚሰጣቸው ጉዳይ መኾኑን ነው የገለጹት።
ባልተመቻቸ የሥራ ኹኔታ የነበሩ ዜጎችን የመመለስ ሥራም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል። ኢትዮጵያ በዓባይ እና በቀይ ባሕር መካከል የምትገኝ ሀገር ናት ያሉት ፕሬዝዳንቱ እጣ ፋንታዋ እና መጻኢ እድሏም ከሁለቱ ውኃዎች ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ፍትሕን ባልተከተለ፣ ሕዝብን ባላማከለ እና ባላሳተፈ መንገድ ተገልላ ቆይታለች ነው ያሉት። ኢትዮጵያ ወደ እነዚህ ውኃዎች እንድትመለስ እና ፍትሐዊ የልማት ተጠቃሚ እንድትኾን መንግሥት እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
ከሦስት አሥርት ዓመታት በኋላ የባሕር በር ጉዳይ ዓለም አቀፍ የመነጋገሪያ ሃሳብ ማድረግ መቻሉን ነው የተናገሩት። በቀጣይነትም የቀጣናውን የጋራ የመልማት ፍላጎት ያገናዘበ ትብብር እና ትስስር ለማጠናከር ዲፕሎማሲያዊ እና የሰላም ጥረቶች እንደሚዳረጉ ገልጸዋል።
መንግሥት ፍትሐዊ እና አስተማማኝ የባሕር በር ለማግኘት ከቀጣናው ሀገራት ጋር በሰላማዊ መንገድ እንደሚሠራም አስታውቀዋል። መንግሥት በውጭ ጉዳይ ፖሊሲው ቅድሚያ ለጎረቤት የሚለውን መርሕ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።
ባለፉት ዓመታት ከጎረቤት ሀገራት ጋር ትብብር ለማድረግ ጥረት መደረጉንም ተናግረዋል። ችግሮችን በመልካም ጉርብት እና ለመፍታት ጥረት ሲደረግ መቆየቱንም ገልጸዋል።
መንግሥት የጀመራቸውን ትብብሮች አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል። አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እንደሚሠራም አስታውቀዋል።
በዓለም አቀፍ የኃይል አሠላለፍ ውስጥ ሚዛኑን በመጠበቅ ትብብርን እና የጋራ ተጠቃሚነትን ለማስፋት ይተጋል ነው ያሉት። በዓለም መድረኮች የኢትዮጵያ ተሳትፎ እና ተደማጭነት እንዲያድግ፣ በዓለም ወሳኝ ጉዳይ ላይ ጉልህ ሚና እንዲኖራት በትኩረት እንደሚሠራም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በበርካታ ፈተናዎች ውስጥ እያለፈ በላቀ ትጋት ዘርፈ ብዙ እና አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ገልጸዋል።
ውጤቶችም የኢትዮጵያን ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ እና ጂኦ ስትራቴጂካዊ ቁመና በማሻሻል የቀደመው የታዛቢነት ታሪክ ማብቂያ፣ አዲስ የታሪክ መክፈቻ እና የኢትዮጵያ ማንሠራራት ብሥራት ይኾናሉ ነው ያሉት።
ስኬቶችን በማስፋት እና በማጎልበት የኢትዮጵያን እድገት ወደ ማይቀለበስ ምዕራፍ እንዲሸጋገር እንደሚሠራም ተናግረዋል። ኢትዮጵያ በአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት እንድትኾን መንግሥት አበክሮ ይሠራል ብለዋል።
ሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ፍትሐዊ፣ ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊ እና በኢትዮጵያውያን ዘንድ ተዓማኒ ይኾን ዘንድ መንግሥት ይሠራል ብለዋል።
መላው ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያ የጀመረቻቸውን የለውጥ እርምጃዎች አበርትተው እንዲደግፍም ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ወዳጆች እና የብልጽግናዋ አጋሮች ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም የስኬቱ ሁነኛ አጋዥ እንዲኾኑ ጥሪ አቅርበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“መንግሥት የማኅበራዊ አገልግሎት መስጫዎችን ለማዘመን እና ለማስፋፋት ይሠራል” ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ
Next article“ዘላቂ ሰላም የሚመጣው በመነጋገር እና በውይይት መኾኑን መንግሥት በጽኑ ያምናል” ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ