
ባሕር ዳር: መስከረም 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የ2018 ዓ.ም 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ተካሄዷል፡፡
የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ የዲጂታል ኢትዮጵያ ልማት እውን መኾን የሀገሪቱ ፖለቲካዊ ትስስርን ያዘምነዋል ብለዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ የዲጂታል ቴክኖሎጂን በማስፋት እና አገልግሎቱን ተደራሽ በማድረግ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ይደረጋል ነው ያሉት፡፡
በ2018 በጀት ዓመት ዜጎች የዲጂታል መታወቂያ ባለቤት ለማድረግ በስፋት ይሠራል፤ የዲጂታል ዘርፉ ለሌሎች ዘርፎችም አስቻይ እንዲኾን ይደረጋል ብለዋል፡፡
ሀገሪቱ ለማዕድን ዘርፍ ትኩረት በመስጠት እሴት የተጨመረባቸው የማዕድን ምርቶችን ለገበያ እንዲቀርቡ ታደርጋለች ነው ያሉት፡፡ አዳዲስ የማዕድን ልማት ሥራዎችም በክትትል ይጠናከራል ብለዋል፡፡
መንግሥት በትራንስፖርት፣ በኢነርጅ፣ በመስኖ፣ በታዳሽ ኀይል እና ውኃ ዘርፎች በትኩረት ይሠራል ነው ያሉት፡፡
ፕሬዝዳንቱ ኤሌክትሪክን በመላ ሀገሪቱ እንዲስፋፋ ይደረጋል ብለዋል፡፡ ለሌሎች ሀገራት ሽያጭ የሚበቃ ኤሌክትሪክ በማምረትም ለቀጣናው ሀገራት ይቀርባል ነው ያሉት፡፡ ታዳሽ ኀይል እንደሚስፋፋም ነው ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ የተናገሩት፡፡
ቴሌ ኮሙኒኬሽንን በማስፋፋት ለመላው ማኅበረሰብ ይደርሳል ያሉት ፕሬዝዳንቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ የንጹህ የመጠጥ ውኃ ሽፋንም ይስፋፋል ብለዋል።
የትምህርት ጥራትን ለመጠበቅ መንግሥት ደረጃቸውን የጠበቁ ቅድመ እና መደበኛ ትምህርት ቤቶችን ያስፋፋል፡፡ የቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጆችንም ያዘምናል ነው ያሉት፡፡
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአካዳሚክ ነጻነታቸው ተጠብቆ እንዲሠሩ ይደረጋል ያሉት ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በአርብቶ አደር አካባቢ የትምህርትን ተደራሽነተት ለማስፋፋት በልዩ ሁኔታ ይሠራል ነው ያሉት፡፡
የጤና ተቋማትን በማስፋፋት ወረርሽኞችን መከላከል የሚያስችል ልዩ ሥርዓት ይዘረጋልም ብለዋል፡፡
በ2018 በጀት ዓመት የኢትዮጵያ የመንገድ አውታር ሽፋን ለማሳደግ ይሠራል ያሉት ፕሬዝዳንቱ የአየር ትራንስፖርት መዳረሻዎች ይስፋፋሉ፤ የባቡር ትራንስፖርትም ይዘምናል ነው ያሉት፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን