ኢትዮጵያ በመጀመሪያ ደረጃ ጤና ክብካቤ የተሻለ ሥራ ሠርታለች።

2
አዲስ አበባ፡ መስከረም 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሁለተኛው ዓለም አቀፍ የጤና እንክብካቤ ኮንፈረንስ እየተካሄደ ነው።
ኮንፈረንሱ “በ 21ኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪያ ደረጃ የጤና እንክብካቤን ማሳደግ እና ሰውን ማስቀደም” በሚል መሪ መልዕክት ከ64 በላይ ሀገራት የተውጣጡ ተሳታፊዎች በተገኙበት ነው በአዲስ አበባ እየተካሄደ የሚገኘው።
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት የማኅበረሰቡን ጤና የሚያሻሽሉ ሥራዎችን ስትተገብር መቆየቷን ገልጸዋል።
በዚህ ሂደት የእናቶችን የወሊድ ሞት ምጣኔ በመቀነስ እና የጤና ተቋማት ተደራሽነትን በማስፋፋት እረገድ የመጀመሪያ ደረጃ ጤና ክብካቤ የራሱ አበርክቶ ነበረው ብለዋል።
ከአጋር እና ባለድርሻ አካላት ጋር በመኾን የማኅበረሰቡን ፍትሐዊ የጤና ተጠቃሚነት ለማስፋትም የተለያዩ ለውጦች መተግበራቸው እንደሚቀጥልም ነው የተናገሩት።
የመጀመሪያ ደረጃ ጤና ክብካቤ በጤናው ዘርፍ ብቻ ሳይኾን የመንግሥት የልማት ግብ አጀንዳ ተደርጎ እየተሠራበት መኾኑንም ገልጸዋል።
የዓለም አቀፉ የመጀመሪያ ደረጃ ጤና ክብካቤ በኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብነት ዘለቀ ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ የመጀመሪያ ደረጃ ጤና ክብካቤን ለማኅበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት ሲተገበር መቆየቱን አብራርተዋል።
በዚህም በመረጃ ላይ የተመሠረተ የጤና ሥርዓትን መገንባት፣ የውስጥ ፖሊሲዎችን ማሻሻል፣ የጤና ባለሙያዎችን አቅም ማጎልበት እና ማኅበረሰብ ተኮር የጤና ተደራሽነትን ማስፋት ላይ ውጤታማ ሥራ መሥራት ተችሏል ብለዋል።
ኮንፈረንሱ ከሃሳብ ልውውጥ የተሻገረ አጋርነትን በመመሥረት ዘላቂ የጤና ክብካቤን ለመተግበር መንቀሳቀስ ይገባልም ብለዋል።
በዓለም የጤና ድርጅት የአፍሪካ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር መሐመድ ጃናቢ ኢትዮጵያ በመጀመሪያ ደረጃ ጤና ክብካቤ የተሻለ ሥራ ሠርታለች ብለዋል።
በቅርቡ ሀገሪቱ ሦሥተኛውን የፋርማሲዮቲካል የብቃት ቁጥጥር ካሳኩ ዘጠኝ የአፍሪካ ሀገራት አንዷ መኾን መቻሏን ለማሳያነት አንስተዋል።
ሀገራት የጤና ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የመጀመሪያ ደረጃ የማኅበረሰብ ጤና ክብካቤ ላይ ትኩረት አድርገው መሥራት እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል።
በኮንፈረንሱ ከተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ ከ705 በላይ ተሳታፊዎች የተገኙ ሲኾን ለተከታታይ አምስት ቀናት በተለያዩ ኹነቶች ኮንፈረንሱ እንደሚቀጥልም ተገልጿል።
ዘጋቢ፦ ቤተልሄም ሰለሞን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“የውጭ ግንኙነታችን ማጠንጠኛው ብሔራዊ ጥቅም እና የዜጎች ክብር ነው” ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ
Next articleየተቀናጀ የፖሊዮ ወረርሽኝ የዘመቻ ክትባት ሊሠጥ ነው።