“የውጭ ግንኙነታችን ማጠንጠኛው ብሔራዊ ጥቅም እና የዜጎች ክብር ነው” ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ

4
ባሕር ዳር: መስከረም 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌደሬሽን ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የጋራ መክፈቻ ሥነ ሥርዓት እየተካሄደ ነው።
ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ የፌደራል መንግሥቱን ዓመታዊ ዕቅድ አቅርበዋል።
በ2017 በጀት ዓመት በማኅበራዊ ዘርፍ በርካታ ውጤቶች መገኘታቸውን ገልጸዋል። የእሴት መሸርሸር ዋነኛ መነሻው የትምህርት ጥራት ችግር እንደኾነ መንግሥት ያምናል ያሉት ፕሬዝዳንቱ ይህን ሳንካ ለመቅረፍ ለትምህርት ጥራት ትኩረት ተደርጓል ነው ያሉት።
ትምህርት ለትውልድ በሚል መሪ መልዕክት የትምህርት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ መሠራቱንም ገልጸዋል። የተማሪዎች ምገባ መካሄዱንም ተናግረዋል። በጤናው ዘርፍም በሽታን ከመከላከል ባለፈ አክሞ በማዳን ላይ ትኩረት ማድረጉን ገልጸዋል።
መሠረታዊ የጤና አገልግሎት ከመስጠት ባሻገር የሕክምና ማሣሪያዎችን እና መድኃኒቶችም በሀገር ውስጥ በማምረት ከፍተኛ ውጤት መገኘቱን ነው የተናገሩት።
የወጣቶችን አዕምሯዊ እና አካላዊ ብቃት ለማሳደግ መሠራቱንም ገልጸዋል።
“የውጭ ግንኙነታችን ማጠንጠኛው ብሔራዊ ጥቅም እና የዜጎች ክብር ነው” ያሉት ፕሬዝዳንቱ የኢትዮጵያ የጂኦ ስትራቴጂካዊ ቁመና በመደርጀት ላይ ይገኛል ብለዋል። ከታዛቢነት ወደ አጀንዳ ተላሚነት እና ተጽዕኖ ፈጣሪነት ለማሸጋገር አስችሏል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ በድንበር ተሻጋሪ ሃብቶቿ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ስትቀበል በዛው ልኬታም አስተማማኝ የባሕር በር የማግኘት መብቷን ማረጋገጥ ይኖርባታል ብለዋል።
የኢትዮጵያ የሕልውና መሠረት በኾኑት በሁለቱ ታላላቅ የውኃ ሃብቶች ዙሪያ መንግሥት ያልተቋረጠ ሰላማዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ጥረት በማድረግ ላይ መኾኑን ገልጸዋል።
እስካሁን በተደረጉ ጥረቶች ሦሥት ጉልህ ውጤቶችን ማስመዝገብ ተችሏል ያሉት ፕሬዝዳንቱ አንደኛው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አጋጥሞት የነበረውን ፈተናዎች በጥበብ በማለፍ ማጠናቀቅ ተችሏል። አስተማማኝ እና ዘላቂነት ያለው የባሕር በር የማግኘት ጉዳይ ከፍ ወደ አለ ደረጃ ተሸጋግሯል፤ ይህ ፍትሐዊ ጥያቄም በዓለም አቀፉ ማኅበረሰቡ ዘንድ እያደገ የመጣ ቅቡልነት ማግኘት ችሏል። በውጭ ሀገር ለእንግልት የተጋለጡ ዜጎች በክብር ተመልሰዋል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ ቁልፍ የታሪክ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች ብለዋል። ዛሬ የምናከናውናቸው ተግባራት የሀገራችንን የቀጣይ ዘመን እጣ ፋንታ ይወጥናሉ፤ አሁን ያለንበት ጊዜ ተገቢው ልኬታ እና ወቅቱ በሚጠይቀው ብልሃት መጠቀም መቻላችን መጻዒው ዘመንን አስተማማኝ እና በታሪክ የሚዘከር እንደሚያደርገው እሙን ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የሕልውና አደጋ እና በርካታ ፈተናዎችን ተሻግራ ጠንካራ አቅም መገንባቷንም ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous article“የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ2017 በጀት ዓመት 8 ነጥብ 8 በመቶ አድጓል” ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ
Next articleኢትዮጵያ በመጀመሪያ ደረጃ ጤና ክብካቤ የተሻለ ሥራ ሠርታለች።