“የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ2017 በጀት ዓመት 8 ነጥብ 8 በመቶ አድጓል” ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ

1
ባሕር ዳር: መስከረም 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የጋራ መክፈቻ ሥነ ሥርዓት እየተካሄደ ነው።
ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ የፌደራል መንግሥቱን ዓመታዊ ዕቅድ እያቀረቡ ነው።
በአዲሱ ዓመት መባቻ የበርካታ ዓመታት ቁጭታችን የጥረታችን ውጤት የኾነውን የሕዳሴ ግድብ ያስመረቅንበት፣ በወርሐ መስከረም መጀመሪያ ላይ የኢትዮጵያ የከርሰ ምድር ሃብት የብስራት ጅማሮ የኾነውን የተፈጥሮ ጋዝ ያወጣንበት እና የዕድገታችን መልሕቅ የኾኑ ፕሮጀክቶችን የጀመርንበት በመኾኑ ይህ ዘመን በታሪካችን ውስጥ በጉልህ የሚነሳ አዲስ ምዕራፍ ሊኾን እንደሚችል አልጠራጠርም ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚን የሚያሻሻል ሥራ መሠራቱንም ገልጸዋል። መንግሥት የኢኮኖሚ መዛባትን የሚያርሙ እና ወደ ብልጽግና የሚያሳድጉ ፈጣን ማሻሻያ ማድረጉን ተናግረዋል። የልማት አቅጣጫው ወደ ባለብዙ ኢኮኖሚ መሸጋገሩንም አንስተዋል።
መንግሥት ኢኮኖሚውን ከዕዳ ጥገኝነት በማላቀቅ ወደ ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነት ለማሸጋገር የሚያስችል ወሳኝ ምዕራፍ ከፍቷል ነው ያሉት። የኢኮኖሚ መሠረቱ ያሉትን አቅም ማወቅ፣ በችግር ውስጥ ዕድልን ማየት፣ በፈጠራ እና በፍጥነት፣ በትብብር እና የተለያዩ አቅሞችን በማሰባሰብ ላይ ያተኮረ ነው ብለዋል።
ከዕዳ ጫና በመላቀቅ በራስ አቅም ችግርን በመፍታት፣ ከአግላይ የኢኮኖሚ ሥርዓት ወደ አሳታፊ እና ምቹ የኢኮኖሚ ምሕዳር መሸጋገሩን ተናግረዋል። የሕዝብን አኗኗር ለመለወጥ እና ዘላቂ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ጥረት መደረጉን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ2017 በጀት ዓመት 8 ነጥብ 8 በመቶ ማደጉንም ተናግረዋል። በ2017 የምርት ዘመን 1 ነጥብ 57 ቢሊዮን ኩንታል ምርት መመረቱን አስታውቀዋል። ይህም ከቀደመው ዓመት 24 ነጥብ 7 በመቶ ብልጫ አለው ነው ያሉት።
የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም ከ59 በመቶ ወደ 65 በመቶ ማደጉን ገልጸዋል። በኢትዮጵያ ከ150 በላይ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶች መካሄዳቸውን ገልጸዋል። የዲጂታል ኢኮኖሚ በከፍተኛ ሁኔታ እድገት ማሳየቱን ተናግረዋል።
በ2017 በጀት ዓመት 8 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር ከወጪ ንግድ መገኘቱን ገልጸዋል። ይህም በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ መኾኑን ተናግረዋል። የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ በተደረገው ተከታታይ ጥረት ለውጥ መገኘቱን አንስተዋል። ለመንግሥት ሠራተኞች የደሞዝ ማሻሻያ መደረጉንም ተናግረዋል።
በ2017 በጀት ዓመት መንግሥት ከብሔራዊ ባንክ ምንም ዓይነት የቀጥታ ብድር ሳይወስድ የበጀት ዓመቱን አጠናቅቋል ነው ያሉት። ይህም ትልቅ ጉዳይ መኾኑን ነው የተናገሩት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleመምህራን ትውልድ ቀራጮች ብቻ ሳይኾኑ የሀገር “አርክቴክቶችም” ናቸው።
Next article“የውጭ ግንኙነታችን ማጠንጠኛው ብሔራዊ ጥቅም እና የዜጎች ክብር ነው” ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ