“ተቋማዊ ሪፎርሙ ወቅታዊ ችግርን ተሻግሮ መጻዒውን ጊዜ ታሳቢ ያደረገ ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

10
ባሕር ዳር: መስከረም 25/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የጀመረውን የሪፎርም ሥራ ዲጂታላይዜሽን ማብሰሪያ እና የአዲስ ሕንጻ ምረቃ መርሐ ግብር እያካሄደ ነው።
በመርሐ ግብሩ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደን ጨምሮ ሌሎች የፌደራል እና የክልል ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ላለፉት ዓመታት ክልሉ የገጠመውን ግጭት ተሻግሮ አንጻራዊ ሰላም እንዲያገኝ የክልሉ እና የፌደራል የፀጥታ ኃይሎች ዋጋ ከፍለዋል ብለዋል።
የተቋማት ሪፎርም አስፈላጊ የኾነውም ክልሉ ካጋጠመው ፈተና ዘላቂ መፍትሔን ለማመንጨት ነው ብለዋል።
ሪፎርሙ የፀጥታ ኃይላችን የሚሰማራባቸውን እና የሚሰለጥንባቸውን ቦታዎች ማሻሻል እና ማዘመንን ማዕከል ያደረገ ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ የሰው ኃይል አቅምን ማሳደግ፣ ምቹ የሥራ አካባቢን መፍጠር እና ዘመኑን የሚመጥን ቴክኖሎጂ መታጠቀን ታሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል።
እስካሁን ባለው የሪፎርም ሥራ የቴክኖሎጂ ልምምዱ አቅም በፈቀደ መልኩ ተስፋ ሰጪ መኾኑን አንስተዋል። የተጀመረው የሰው ኃይል ልማት በሚፈለገው መንገድ እየሄደ ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ በቀጣይ ሙያዊ ሥነ ምግባርን እና የላቀ ግዳጅ አፈጻጸምን ማሻሻል ያስፈልጋል ብለዋል።
በክልሉ አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን መሥራት ያስፈልጋል ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ “ተቋማዊ ሪፎርሙ ወቅታዊ ችግርን ተሻግሮ መጻዒውን ጊዜ ታሳቢ ያደረገ ነው” ብለዋል።
ርእሰ መሥተዳድሩ ተቋማዊ ለውጡ እስከ ታችኛው የፖሊስ መዋቅር ድረስ እንዲደርስ የክልሉ መንግሥት ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል። በሪፎርም ሥራዎቹ የላቀ አበርክቶ ያላቸውን ተቋማት እና ግለሰቦች በክልሉ መንግሥት ሥም አመስግነዋል።
ዘጋቢ፦ ታዘብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“ፖሊስ ልቡ፣ አስተሳሰቡ እና እጁ ከጽንፈኝነት፣ ጎጠኝነት እና ሌብነት የፀዳ መኾን ይኖርበታል” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ