
መስከረም 25/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የጀመረውን የሪፎርም ሥራ ዲጂታላይዜሽን ማብሰሪያ እና የአዲስ ሕንጻ ምረቃ መርሐ ግብር እያካሄደ ነው።
በመርሐ ግብሩ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የፌደራል እና የክልል ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
ትናንት “ኢትዮጵያ ትቀጥላለች አትቀጥልም” ትንቅንቅ ውስጥ በነበርንበት ወቅት ሁሉ የፀጥታ ኀይሉ ውድ ዋጋ ከፍሏል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የዛሬው ሪፎርም የትናንቱ ብርቱ ተጋድሎ ውጤት እንደኾነም ጠቁመዋል።
ኤርጎኖሚክስ የለውጡ መንግሥት አንዱ የትኩረት መስክ ነበር ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምቹ የሥራ አካባቢ መፍጠር ለውጥ ከራስ ጽዳት ይጀምራል ከሚል እሳቤ የመነጨ እንደኾነም አንስተዋል። በክልሉ በርካታ ተቋማት የሚታየው የለውጥ ጅምርም አበረታች ነው ብለውታል።
የክልሉ ሕዝብ በሁለት የትውልድ መንታ ተጋድሎ ላይ የሚገኝ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባዕዳ እና ባንዳን የማጽዳት እና ድህነት እና ኋላቀርነትን ታሪክ የማድረግ ትግል እንደኾነም አንስተዋል።
የአማራን ሕዝብ ከኢትዮጵያዊነት ማማ እና ካስማ ለማውረድ የሚደረገው ሙከራ ትናንት እንዳልተሳካ ታይቷል፤ ዛሬም አልተሳካም፤ ነገም አይሳካም ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በእያንዳንዷ እኩይ ተግባራቸው የክልሉን ሕዝብ ዋጋ ማስከፈላቸው ግን አልቀረም ነበር ነው ያሉት።
የለውጥ ሥራዎቹ አስፈላጊነትም የክልሉን ዘላቂ እና አስተማማኝ ሰላም ባጠረ ጊዜ ለማምጣት ያለመ ነው ብለዋል።
መለዮለባሽ ተጠሪነቱ ሕዝብ ለመረጠው አካል ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ከዚያ ሲያፈነግጥ ግን ምን ዓይነት ዋጋ እንደሚያስከፍል ብዙም ሳንርቅ ትናንት ከራሳችን ዛሬ ደግሞ ከጎረቤቶቻችን አይተናል ነው ያሉት።
ተቋሙ ከለውጥ ሥራዎቹ ጎን ለጎን ክልሉን ከቀሪ ባዕዳ እና ባንዳዎች ማጽዳት ይኖርበታል ብለዋል። ዛሬ የፀዳ እና ምቹ የሥራ አካባቢ ያሳየን የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ በቀጣይም ላመነበት ቃል እና ተልዕኮ መስዋዕትነት መክፈልን የሚደፍር፤ ለሕዝብ ክብር ሲባል ራሱን ቅድሚያ የሚያሳልፍ ሠራዊት መገንባት ግድ ይለዋል ነው ያሉት።
ክልሉን የሚመጥን ፖሊስ መገንባት የቀጣይ ጊዜ ተልዕኮ ነው፤ ጠላት የሚፈራው እና ሕዝብ የሚመካበት የፖሊስ ሠራዊት መገንባት አለበት ነው ያሉት።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው ፖሊሰ በትንሽ በትልቁ እጅ መንሻ ከፈለገ መለዮውን ረስቶታል ማለት ነው ብለዋል። “ፖሊስ ልቡ፣ አስተሳሰቡ እና እጁ ከጽንፈኝነት፣ ጎጠኝነት እና ሌብነት የፀዳ መኾን ይኖርበታል” ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን