“ተቋማዊ ሪፎርሙ የክልሉ ፖሊስ የተደራጁ ወንጀሎችን እና የፀረ ሰላም ኃይሎችን እንቅስቃሴ በቀላሉ ለመከላከል የሚያስችል አቅም እየፈጠረ ነው” ኮሚሽነር ዘላለም መንግሥቴ (ዶ.ር)

16
ባሕር ዳር: መስከረም 25/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የጀመረውን የሪፎርም ሥራ ዲጂታላይዜሽን ማብሰሪያ እና የአዲስ ሕንጻ ምረቃ መርሐ ግብር እያካሄደ ነው።
በመርሐ ግብሩ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የፌደራል እና የክልል የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
ፖሊስ የአሠራር ነጻነት እንዲኖረው እና ተጠሪነቱ ለምክር ቤቱ እንዲኾን መደረጉ ለለውጥ ሥራዎች መሠረት ጥሏል ያሉት የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ዘላለም መንግሥቴ (ዶ.ር) ይህም ሠራዊቱ ሙያውን አክብሮ እንዲያስከብር የሚያስችሉ ሥር ነቀል ለውጦችን ለማምጣት አግዟል ብለዋል።
ተቋማዊ ሪፎርሙን ተከትሎም የክልሉ ፖሊስ የተደራጁ ወንጀሎችን እና የፀረ ሰላም ኃይሎችን እንቅስቃሴ በቀላሉ ለመከላከል የሚያስችል አቅም እየፈጠረ ነው ብለዋል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በክልሉ የተከሰተው የፀረ ሰላም ኃይሎች እኩይ ተግባር ዘርፈ ብዙ ችግሮችን አስከትሏል ያሉት ዋና አዛዡ ችግሩን በውስጥ አቅም ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሠሩ ነው ብለዋል። “ፖሊስ ሕዝባዊ ቅቡልነት እንዲኖረው እየተደረገ ያለው ጥረት ለውጥ እያሳየ ነውም” ብለዋል።
በሪፎርም ሥራዎች ቴክኖሎጅ መር ዘመናዊ ወንጀል ምርመራ ሂደት እንዲጠናከር እየተሠራ መኾኑንም ዋና አዛዡ ጠቁመዋል።
የክልሉ ፖሊስ የሪፎርም ሥራዎች በሕግ ማስከበር ወቅት ጉዳት የደረሰባቸውን አባላት በዘላቂነት መደገፍ የሚያስችል አሠራር መዘርጋት፣ የጀግኖች ማዕከል ግንባታ እና የፖሊስ ኮሌጅን ደረጃ ማሳደግ የሪፎርም ሥራዎቹ አካል ናቸው ብለዋል።
ከ3 ሺህ 700 በላይ የፖሊስ ሠራዊት አባላት የሹመት ዕድገቶች ይሰጣሉ ያሉት ኮሚሽነሩ ይህም ለላቀ የግዳጅ አፈጻጸም እና መዋቅራዊ ሪፎርም መሳካት አጋዥ ነው ብለዋል።
ዋና አዛዡ ኮሚሽነር ዶክተር ዘላለም መንግሥቴ የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አሁን ካለበት የለውጥ ቁመና ላይ እንዲደርስ በርካቶች ውድ ዋጋ ከፍለዋል ነው ያሉት። ተቋሙን በብቃት የመሩ የቀድሞ ኮሚሽነሮች ተመስጋኝ ናቸውም ብለዋል።
የሪፎርም ሥራዎቹ እንዲሳኩ ድጋፍ ላደረጉ አጋዥ አካላት በተቋማቸው ሥም ምስጋና ያቀረቡት ዋና አዛዡ በተለይም የክልሉ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ እና የሥራ ባልደረቦቻቸው ላደረጉት የላቀ ክትትል እና ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
ዘጋቢ፦ ታዘብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበጀግንነት መጠበቅ፤ በሰብዓዊነት ማገልገል
Next articleለብዙ ችግሮች መፍትሔ የሚሰጥ ፕሮጀክት በደብረ ብርሃን ከተማ ሊገነባ ነው።