
ባሕር ዳር: መስከረም 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) መንግሥት በገለጸው መሠረት ከመስከረም ወር ጀምሮ አዲሱ የደሞዝ ጭማሪ ተግባራዊ እንደሚደረግ የፊዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ገልጿል።
የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር መኩሪያ ኃይሌ (ዶ.ር) ለሁሉም ክልሎችና ለሁለቱ ከተማ መሥተዳድሮች የሲቪል ሰርቪስ ቢሮ ኃላፊዎች እና ለሚመለከታቸው አካላት በአዲሱ የመንግሥት ሠራተኞች በደሞዝ ጭማሪና በአበል ክፍያ ላይ መመሪያ አስተላልፈዋል።
የመንግሥት አገልግሎትና አሥተዳደር ፖሊሲ ትግበራ የሚያፋጥን የደሞዝና የአበል ማስተካከያ የተደረገው መንግሥት የመክፈል አቅም ኖሮት ሳይሆን የመንግሥት ሠራተኛውን የኑሮ ጫና ስለሚያውቅ ትልቅ ዋጋ ተከፍሎ ይህ ጭማሪ እንደተደረገ ተናግረዋል።
ሠራተኛው ይህን ተረድቶ ሕዝቡን በቅንነት በታማኝነት ማገልገል አለበት ያሉት ኮሚሽነሩ ተገልጋዩን ሳያጉላላ ሥራውን መከወን አምራች ኀይል መሆን እንደሚገባው ማሳሰባቸውን የዘገበው ኢቢሲ ነው።
ደሞዙ ከመስከረም 01/2018 ዓ.ም ጀምሮ ይከፈላል ያሉት ኮሚሽነሩ ክልሎች ማንኛውንም ጫና በመቋቋም ለሠራተኛው ከዚህ ወር ጀምሮ አዲሱን የመግሥት ሠራተኞች ደሞዝ መክፈል እንዳለባቸው ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!