“መንግሥት ኢትዮጵያን ወደሚገባት ከፍታ ለማውጣት የብልጽግና ጉዞዉን እያሳመረ ቀጥሏል” የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት

17
ባሕር ዳር፡ መስከረም 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) መንግሥት ቃልን በተግባር በመግለጽ የኢትዮጵያን የማንሠራራት ጉዞ እያሳካ መኾኑን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት አስታውቋል።
የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ባወጣው መግለጫ
መንግሥት ከለውጡ እውን መሆን ጀምሮ የገባቸውን ቃሎች እየፈጸመ፣ ኢትዮጵያን ወደሚገባት ከፍታ ለማውጣት የብልጽግና ጉዞውን እያሳመረ ቀጥሏል ብሏል።
ከዓመታት በፊት በ2018 ዓ.ም ከተስፋ ብርሃን ወደሚጨበጥ ብርሃን ሽግግር እናደርጋለን የሚል የሚል ርዕይ የያዘው ቃል የኢፌዴሪ መንግሥት ቃሉን በተግባር እየገለጸ ይገኛል ነው ያለው።
የምግብ ሉዓላዊነታችንን ለማረጋገጥ ብዙ ርቀት ተጉዘናል፤ በመኸር እርሻ፣ በሌማት ትሩፋት፣ በአረንጓዴ ዐሻራ እና በበጋ መስኖ በመታገዝ ሰፋፊ ድሎች ተመዝግበዋል ብሏል።
የከተሞቻችን ገጽታ ለመቀየር በተሠሩ ሥራዎች ከ70 በላይ ከተሞች ገጽታቸዉ በእጅጉ ተለውጧል፡፡ የከተሞቹ የፍሳሽ አወጋገድ ሥርዓት፣ የእግረኛ እና ተሽከርካሪ መንገድ አጠቃቀም፤ እንደ ውኃ፣ ስልክ፣ ኤሌክትሪክና መሰል አገልግሎቶች መሥመር ዝርጋታ በከተሞች የኮሪደር ሥራ በእጅጉ እንዲዘምኑ ተደርጓል፤ እየተደረገም ነው ነው ያለው።
የሥነ ንጽሕና እሳቤ እና ሥርዐት በእጅጉ እየተሻሻለ መጥቷል፡፡ አዲስ አበባን ጨምሮ ከተሞቻችን የአፍሪካ ተምሳሌት ለማድረግ እየተሠራ ነው፡፡
በታዳሽ ኃል አቅርቦት ረገድ ለማሳካት የተቀመጠዉን ግብ ታላቅ የትርክት ለውጥ በፈጠረዉ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አማካኝነት እውን ሆኗል፡፡ ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካና ለሌላዉ ዓለም ያለሰባራ ሳንቲም የውጭ ዕርዳታ በጋራ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ማሳካት እንደሚቻል ሕዳሴ ግድብ ትዕምርታችን ነው፡፡
በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ምርቃት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ሌሎች የገዘፉ ፕሮጀክቶች እንደሚጀመሩ፣ በመጠናቀቅ ላይ የነበሩም እንደሚመረቁ ቃል መግባታቸዉ ይታወሳል፡፡
እነሆ የኢትዮጵያን የማንሠራራት ጉዞ የሚፋጥኑ እንደ ተፈጥሮ ጋዝ ማምረቻ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ተመረቁ፤ ከተመረቀዉ በብዙ እጥፍ ፕሮጀክት ተበሰረ፤ የነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካ እና የዐፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ ፕሮጀክቶች ግንባታ ተጀመሩ ብሏል።
ኢትዮጵያ የኑክሊየር ኃይልን ለሰላማዊ ልማት ለመጠቀም ስምምነቶችን ተፈራረመች፤ ከዓለማቀፍ ተቋማትም ይሁንታን ተቸረች፡፡ እነዚህ ሁሉ ቃልን በተግባር የመለወጥ ልምድ የወለዳቸው፤ የሕዝብ እና ዓለማቀፍ ተቋማትን እምነት ማግኘት የተቻለባቸው የመንግሥት ጥረት ውጤቶች ናቸው፡፡
መንግሥታችን አሁንም በተመዘገቡ ስኬቶች ረክተው የሚተኛ መንግሥት አይደለም። የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ ከስር ከስር እያሳካ አዳጊ ፍላጎቶችን እያዋለደ ለላቀ ብልጽግና መትጋቱን ይቀጥላል፡፡
ከመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው ለትውልድ ምንዳን እንጅ ዕዳን አናወርስም ባለዉ መሠረት በልጆቿ የጋራ ጥረት የበለጸገችና በምሳሌነት የምትጠቀስ ኢትዮጵያን የመገንባቱ ጥረት በላቀ ፈጠራ፣ ፍጥነት እና ትጋት ይቀጥላል ብሏል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“ከዛሬ ጀምሮ ነዳጅ የሚጠቀሙ ማንኛውም ከባድ ተሽከርካሪዎች (ትራክ) ወደ ኢትዮጵያ ማስገባት የተከለከለ ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next articleከመስከረም ወር ጀምሮ አዲሱ የደሞዝ ጭማሪ ተግባራዊ ይደረጋል።