“ከዛሬ ጀምሮ ነዳጅ የሚጠቀሙ ማንኛውም ከባድ ተሽከርካሪዎች (ትራክ) ወደ ኢትዮጵያ ማስገባት የተከለከለ ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)

25
ባሕር ዳር: መስከረም 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በሶማሌ ክልል ካሉብ በዓመት 111 ሚሊዮን ሊትር ማምረት የሚችለውን የኦጋዴን ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጀክት የመጀመሪያ ዙር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በተገኙበት ተመርቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምርቃቱ ወቅት እንደተናገሩት ፕሮጀክቱ ለኀይል ማመንጫ እና ለክሪፕቶ ማይኒንግ ሥራዎች አስፈላጊ የሆኑ ግብአቶችን ጭምር የሚያቀርብ መሆኑን ገልጸዋል።
ቢበዛ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ 2 ሺህ የሚጠጉ የአዲስ አበባ ከተማ እና ወደ ክልል የሚሄዱ አውቶቢሶች አሁን ከሚጠቀሙት ነዳጅ ወደ ጋዝ እንቀይራለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህም የትራንስፖርት ወጪ በ50 በመቶ የሚቀንስ መሆኑን አስረድተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
ቢበዛ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ 2 ሺህ የሚጠጉ የአዲስ አበባ ከተማ እና ወደ ክልል የሚሄዱ አውቶቦሶች አሁን ከሚጠቀሙት ነዳጅ ወደ ጋዝ እንቀይራለን ብለዋል።
እነዚህ 2 ሺህ መኪኖች ሲቀየሩ የትራንስፖርት ዋጋ ቢበዛ ወይም ቢያንስ አሁን ካለው በ50 በመቶ በሚቀጥለው ዓመት እንቀንሳለን ነው ያሉት።
በከተማ ትራንስፖርት 50 በመቶ አሁን ያለውን ዋጋ ቀነስን ማለት በአነስተኛ ገቢ ወጥተው የሚገቡ ሠርተው የሚውሉ ዜጎች በእጅጉ ኑሯቸውን ለማገዝ የሚጠቅም እንደሆነም ተናግረዋል።
ሦስተኛ ኀይል ስናመርት ለክሪፕቶ ብቻ ሳይሆን ለብርሃንም ጭምር ስለሆነ ጋዝ ምግባችን፣ ጋዝ ትራንስፖርታችን፣ ጋዝ ለኢነርጂ ማምረቻ የሚውል ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ነው ብለዋል።
ለትናንሽ መኪኖች ከኤሌክትሪክ መኪና ውጪ ማስገባት ታግዶ እንደቆየው ከዛሬ ጀምሮ ነዳጅ የሚጠቀሙ ማንኛውም ትራክ ወደ ኢትዮጵያ መስገባት የተከለከለ መሆኑንም ገልጸዋል።
እንደ ማዕድን ሚኒስቴር መረጃ በአንጻሩ ማንኛውም የግል ባለሃብት ጋዝ የሚጠቀሙ ትራኮች የሚያስገባ ከሆነ ከቀረጥ ነጻን ጨምሮ አስተማማኝ ድጋፍ የሚደረግላቸው እንደሆነ ተመላክቷል። እንደሀገር እየወጣ ያለውን ከፍተኛ ወጪ ለመቀነስና ትራንስፖርትን ለማሳለጥ የግሉ ዘርፍ በጋዝ የሚጠቀሙ ትራኮች በማስገባት የሀገሩን የኢኮኖሚ እድገት እንዲያፋጥንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየምክር ቤቶቹ የጋራ የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት መስከረም 26/2018ዓ.ም ይካሄዳል።
Next article“መንግሥት ኢትዮጵያን ወደሚገባት ከፍታ ለማውጣት የብልጽግና ጉዞዉን እያሳመረ ቀጥሏል” የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት