” መንግሥት በመወጣጫ መደርመስ ምክንያት ባጋጠመዉ አደጋ በደረሰዉ ጉዳት የተሰማዉን ጥልቅ ኀዘን ይገልጻል” የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት

13
ባሕር ዳር: መስከረም 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት በሰሜን ሸዋ ዞን አረርቲ ከተማ አሥተዳደር በደረሰው አደጋ የሀዘን መግለጫ አውጥቷል።
ባወጣው የሀዘን መግለጫ በግንባታ መወጣጫ መደርመስ ምክንያት ባጋጠመዉ አደጋ በደረሰዉ ጉዳት መንግሥት ኀዘኑን ይገልጻል ብሏል።
በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን አረርቲ ከተማ አሥተዳደር በግንባታ ላይ የሚገኝ የማሪያም ቤተክርስቲያን ሕንፃን በመጎብኘት ላይ የነበሩ ሰዎች በደረሰባቸው አደጋ ተጎድተዋል፡፡ ሕይወታቸዉን ያጡ፣ ከባድ እና ቀላል የአካል ጉዳት የደረሰባቸዉ በርካታ ሰዎች መኖራቸዉ በመሰማቱ መንግሥት የተሰማዉን ኀዘን ይገልጻል፤ ለተጎጂ ቤተሰቦች መጽናናትን፤ በሕክምና ላይ ለሚገኙት በፍጥነት ማገገምን እንመኛለን ነው ያለው።
ኢትዮጵያ በሁለንተናዊ ግንባታ ላይ ናት፡፡ ከትልልቅ ግድቦች ጀምሮ እስከ አነስተኛ የግለሰብ ቤት አጥር ድረስ ያሉ ግንባታዎች ሲሠሩ ግን ደኅንነትን ቅድሚያ መስጠት አለባቸው፤ የግንባታ ሕጎቻችንም ይህንኑ ታሳቢ ያደረጉ ናቸው፡፡ በግንባታ ቦታዎች ሁሉ ለሰዎች ደኅንነት ቅድሚያ መስጠት ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ነው፡፡ የግንባታ ቦታዎች ላይ የሚደረጉ ጉብኝቶችም የሥራ ላይ ደኅንነት መርሆዎችን እንዲጠብቁ ማድረግ ይገባል ብሏል።
መንግሥት በድጋሜ በመወጣጫ መደርመስ ምክንያት ባጋጠመዉ አደጋ በደረሰዉ ጉዳት የተሰማዉን ጥልቅ ኀዘን ይገልጻል፡፡ ለተጎጂው ቤተሰቦችና ወዳጆች መጽናናትን ይመኛል ነው ያለው ባወጣው መግለጫ።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የልማት ሥራዎችን ለመጎብኘት ጅግጅጋ ገብተዋል።
Next article” ከጎዳና ላይ ስላነሱን ደስ ብሎኛል” ከጎዳና የተነሳ ታዳጊ