አረጋውያንን መንከባከብ ሀገርን መንከባከብ ነው።

9
አዲስ አበባ: መስከረም 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ዓለም የአረጋውያንን ውለታ ለማውሳት እና በውለታቸው ልክ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ “የአረጋውያንን ቀን” ታከብራለች።
ዘንድሮም ቀኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ35ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ34ኛ ጊዜ እየተከበረ ይገኛል። “ለአረጋውያን ደኅንነት መጠበቅ ሁለንተናዊ ኀላፊነታችንን እንወጣ” በሚል መሪ መልዕክት በሀገር አቀፍ ደረጃ በአዲስ አበባ በጎዳና ላይ ትርኢት እና
በፓናል ውይይት እየተከበረ ነው።
አረጋውያን በጉብዝና ዘመናቸው ለሀገር ጽናት እና ለትውልድ የተሻለ ነገ የበዛ ታሪክ ጽፈዋል።በእርጅና ጊዜያቸውም ልምድ እና ዕውቀታቸውን ተጠቅመው በልማት ተግባራት፣ በሽምግልና፣ በእርቅ በምክር እና ተግሳጽ የተጣመመውን በማረቅ የበዛ ሚናን እየተወጡ የሚገኙ ናቸው።
የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ.ር) በችግር ውስጥ የሚገኙ አረጋውያንን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ደኅንነታቸውን ለማረጋገጥ ሚኒስቴሩ ከሌሎች ተቋማት ጋር ለመሥራት የሚያስችል የአካቶ ትግበራን ጀምሯል ብለዋል።
የማኅበረሰቡን የመረዳዳት እና የመደጋገፍ ግንዛቤን በማሻሻል ለአረጋውያን ተጠቃሚነት መሻሻል በትኩረት እየተሠራ እንደኾነም ገልጸዋል። ባለውለታ የኾኑ እና በችግር ውስጥ ያሉ እናት እና አባቶችን በመጠየቅ እና በመንከባከብ ሁላችንም አደራችን ልንወጣ ይገባል ነው ያሉት።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ የማኅበራዊ ልማት እና የባሕል ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወርቀሰሙ ማሞ አረጋውያን ተነቦ የማያልቅ የታሪክ ማሕደር መኾናቸው ገልጸዋል። “እነሱን መንከባከብ ሀገርን መንከባከብ ጋር እኩል ነው” ብለዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና የማኅበራዊ ልማት፣ የባሕል ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴም ለአረጋውያን የተሻለ ተጠቃሚነት ከባለድርሻ አካላት ጋር በልዩ ትኩረት እንደሚሠራ ገልጸዋል።
በተለይ በጤናው ዘርፍ እና ሌሎች መሠረታዊ አገልግሎቶችን በቀላሉ እንዲያገኙ የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በትኩረት የሚሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አረጋውያን እና ጡረተኞች ብሔራዊ ማኅበር ምክትል ፕሬዝዳንት ጌታቸው ክፍሉ አረጋውያን እና አዲሱ ትውልድ ስለ ሀገር እየተመካከሩ የሚኖሩ ናቸው ብለዋል። አረጋውያን ዕውቀት እና ልምዳቸውን ተጠቅመው ትላንትን አውስተው ለትውልድ የተሻለ ነገ ካሻገሩ አያረጁም ነው ያሉት። ይህ የሀገር እሴት ኾኖ መቀጠል አለበት ብለዋል።
ከ6 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ አረጋውያን እንዳሉ የገለጹት ፕሬዝዳንቱ የበዙት ለዘርፈ ብዙ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግር የተጋለጡ መኾናቸውን ተናግረዋል። ለአረጋውያን የሚገቡ አገልግሎቶችን ተደራሽ ለማድረግ መንግሥታዊ ተቋማት፣ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች እና ሁሉም ኢትዮጵያውያን መልካም ተግባራቸውን ማጠናከር አለባቸው ነው ያሉት።
ዘጋቢ: አዲሱ ዳዊት
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየኢትዮጵያ ሰርኩላር ኢኮኖሚ የፅዱ ኢትዮጵያን ዕሳቤ ለማሳካት ወሳኝ ሚና ይጫወታል።
Next articleየግሸን ደብረ ከርቤ ዓመታዊ የንግስ በዓል በድምቀት እየተከበረ ነው።