
ባሕር ዳር: መስከረም 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የሥነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን የክልሉ ጸረ ሙስና ጥምረት የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸሙን ለመገምገም እና በ2018 በጀት ዓመት ዕቅዱ ላይ ለመወያየት ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ምክክር ጀምሯል።
የአማራ ክልል የሥነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሃብታሙ ሞገስ ኮሚሽኑ የሥነ ምግባር ግንባታን እና የጸረ ሙስና ትግሉን የማስተባበር ሥራ ቢሠራም ሁሉም ተቋም እና ሠራተኞች ኀላፊነት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
የክልሉ ምክር ቤት የተቋማቱን የሥራ እንቅስቃሴ ሥራ በመምራት እና በመገምገም እንደሚመራ ጠቅሰው ኮሚሽኑም በአጋርነት እና በማስተባበር እንደሚሠራ ተናግረዋል።
ባለፈው በጀት ዓመት የጋራ ጥምረት መመሥረቱን እና ሥራዎችን መጀመራቸውን አስታውሰዋል። በዚህ ውይይትም ያለፈውን ገምግሞ ለቀጣይ ዕቅድ በማዘጋጀት በየተቋማቱ ለመሥራት መታሰቡንም አንስተዋል።
የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ እና የጥምረቱ ሠብሣቢ ፋንቱ ተስፋዬ የጥምረቱ ትኩረት በሥነ ምግባር ግንባታ ላይ እና ሃብት ለታለመለት ዓላማ እንዲውል በትኩረት እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
በየተቋማቱ ያለው የጸረ ሙስና ሥራ እንዳልተጠናከረ አመላካቾች እንዳሉ የገለጹት አፈ ጉባኤዋ የጥምረቱ አካላትም ተቋማት በመኾናቸው የሃብት እና የጊዜ አጠቃቀምን በተገቢው መፈተሽ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በተተኳሪ ተቋማት ላይ ያለው የተገልጋዮች ግብረ መልስ እና ቁጥራዊ መረጃዎች የሚያመላክቱት አገልግሎት መስጠት ሳይኾን መሸጥን እንደሚታይ ነው። የተገልጋዮች አገልግሎትን እና ወንበርን የመከራየት ፍላጎት ቀላል አይደለም። ስለዚህ የጥምረቱ አካላት በትኩረት በየተቋማቸው ግንባር ቀደም የጸረ ሙስና ታጋይ መኾን እንደሚገባቸው ነው ያሳሰቡት።
አፈ ጉባኤዋ ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግሥት ለመገንባትም እንቅፋት እየኾነ ያለው አንዱ ሙስና መኾኑን አንስተው መሪዎችም ሕዝብ የሚለውን እየደገሙ መኖር እንደማይገባ አሳስበዋል።
ባለፈው በጀት ዓመት የተከናወነው የጸረ ሙስና ትግል ምዘና መደረጉንም ገልጸዋል። የክልሉ ምክር ቤትም በጥምረቱ ሠብሣቢነቱም ኾነ በክትትል እና ቁጥጥር ሥራው አማካይነት ተቋማትን እየመዘነ መኾኑን አንስተዋል።
በጥምረቱ ውይይትም እያንዳንዱ የጥምረቱ አባል የየራሱን ተቋም ሥራዎች መመዘን እንደሚገባው ተናግረዋል።
የጥምረቱ አባላት ብልሹ ሥነ ምግባር የወለደው ሙስና ፍትሐዊ የሃብት አጠቃቀምን በማዛባት፣ ሰላምን እያደፈረሰ ትውልድን የሚያጠፋ መኾኑን ተረድተው የጥምረቱ አባላት ትግሉን ማጠናከር እንደሚገባቸውም ነው ያሳሰቡት።
ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!