“ኢትዮጵያ ማኅበራዊ ጥበቃን የምትመለከተው እንደ በጎ አድራጎት ብቻ ሳይኾን እንደ መሠረታዊ መብት ጭምርም ነው” ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ.ር)

14
አዲስ አበባ: መስከረም 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ማኅበራዊ ጥበቃ ለዘላቂ ልማት ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ ነው።
የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ.ር) ኢትዮጵያ ልዩ የባሕል ብዝኀነት እና ጠንካራ መንፈስ ያላት ሀገር ብቻ ሳትሆን የሰው ልጅ መፍለቂያ እና የታሪክ መገኛ ጭምር ናት ብለዋል።
በመላው አፍሪካ ወደፊት የሚኖረውን ሁሉን ያካተተ፣ የማይበገር የማኅበራዊ ጥበቃ ሥርዓቶችን በጋራ ለመገንባት ኮንፈረንሱ ወሳኝ መኾኑን ገልጸዋል። ይህ ኮንፈረንስ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በተጠናቀቀበት ጊዜ በኢትዮጵያ መካሄዱ የጎላ ሚና አለው ነው ያሉት።
“ኢትዮጵያ ማኅበራዊ ጥበቃን የምትመለከተው እንደ በጎ አድራጎት ብቻ ሳይኾን እንደ መሠረታዊ መብት እና ለዘላቂ ሀገራዊ ልማት ማበረታቻ የማዕዘን ድንጋይ ጭምርም ነው” ብለዋል ሚኒስትሯ።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያ ለአሕጉሪቱ ጠቃሚ ትምህርቶችን በመስጠት የማኅበራዊ ጥበቃ ተጨባጭ እመርታ አሳይታለች ነው ያሉት።
በተለይም በሴፍቲኔት ፕሮግራም በዓመት ወደ 8 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎችን ይደግፋሉ ብለዋል። ይህም በግብርና፣ በጤና፣ በትምህርት እና በንጽሕና አጠባበቅ ዘርፎች ላይ እንደኾነ ነው ያነሱት።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የከተማ ምርታማ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ለከተሞች መስፋፋት ፈጣን ምላሽ በመስጠት እና ለችግር ተጋላጭ ለኾኑ የከተማ ነዋሪዎች የኑሮ ድጋፍ እና የማይክሮ ፋይናንስ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ነው ያነሱት።
የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከገንዘብ፣ ከጤና፣ ከትምህርት፣ ከከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ጋር ተቀናጅቶ እየሠራ ያለው ተቋማዊ ቅንጅት ጠንካራ እንደኾነም አንስተዋል።
እነዚህ ጥረቶች በአጠቃላይ ድህነትን ለመቅረፍ፣ ሰብዓዊ ካፒታልን ለመገንባት፣ ማኅበራዊ ትስስርን ለማጎልበት እና ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገት ለማምጣት የማኅበራዊ ጥበቃን የመለወጥ አቅምንም ያጎለብታሉ ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ ለተከታታይ አምስት ቀናት የሚቆየው ማኅበራዊ ጥበቃ ለዘላቂ ልማት የአሠልጣኞች ኮንፈረንስ ላይ ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የተወከሉ አምባሳደሮች፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተወካዮች፣ የልማት አጋሮች እና ከኢኮኖሚ ፖሊሲ ጥናትና ምርምር ተቋማት የተወከሉ ተሳታፊዎች ታድመዋል።
ዘጋቢ:- ሰለሞን አሰፌ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleልጅ ከማሕጸን ብቻ ሳይኾን ከልብም ይወለዳል።
Next articleየብሬል እጥረት ዐይነ ስውራን ተማሪዎችን እየፈተነ ነው።