አቢሲኒያ ባንክ ከታክስ በፊት 10 ቢሊዮን ብር በላይ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ።

7
አዲስ አበባ፡ መስከረም 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) አቢሲኒያ ባንክ 29ኛ መደበኛ ጉባኤ እና 16ተኛ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤውን እያካሄደ ነው።
የአቢሲኒያ ባንክ የቦርድ ሊቀመንበር መኮንን ማንያዘዋል እንዳሉት ባንኩ ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጂኦ ፖለቲካዊ ጫናዎችን ተቋቁሞ በተቀማጭ ገንዘብ እና በትርፍ ገቢ አበረታች ውጤት አግኝቷል። በዚህም በ2024/2025 ተቀማጭ ገንዘቡን ወደ 50 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ማሳደግ ተችሏል ብለዋል። በዓመቱም የብድር እና የቅድመ ክፍያ መጠኑ ወደ 193 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር አድጓል ተብሏል። ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ30 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ዕድገት አለው ነው ያሉት። ይህም ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎትን ሳይጨምር መኾኑን ተናግረዋል።
ባለፈው ዓመትም ባንኩ 663 ሚሊዮን ብር የውጭ ምንዛሬ አግኝቷል ነው ያሉት።
ባንኩ በ2024/2025 በጀት ዓመት የ39 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱም ተገልጿል። ከዚህም ውስጥ ከወለድ የተገኘ ገቢ ትልቁን ድርሻ እንደሚይዝም ነው የተብራራው። በዚህም አቢሲኒያ ባንክ በበጀት ዓመቱ ከታክስ በፊት 10 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ያልተጣራ ትርፍ ማስመዝገቡንም ገልጸዋል። ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ91 በመቶ ጭማሪ አለው ብለዋል። ባንኩ አጠቃላይ ሀብቱ 286 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር መድረሱ ተገልጿል። 97 ሚሊዮን ብር ለማኅበራዊ ኀላፊነት ወጭ እንዳደረገም ተመላክቷል።
ዘጋቢ፦ አንዱዓለም መናን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየቅመማ ቅመም ምርት አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እያደረገ ነው።
Next articleቅጥር ማስታወቂያ