
አዲስ አበባ፡ መስከረም 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ድርድር ሂደት 6ኛው የሥራ ቡድን ሥብሠባ በስዊዘርላንድ ጄኔቫ ተካሂዶ በስኬት ተጠናቅቋል።
ይህንኑ አስመልክቶ የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሚኒስትር ካሣሁን ጎፌ (ዶ.ር) ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። ሚኒስትሩ በመግለጫቸው በድርድሩ የተገኘው ስኬት ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ ለድርጅቱ አባልነት መቃረቧን የሚያመለክት ነው ብለዋል።
ከሥራ ቡድኑ አባላት ለተነሱ ከ200 በላይ ጥያቄዎች ምላሽ መሰጠቱን እና ባከናወነው የሥራ ቡድን ሥብሠባ አመርቂ ውጤት የተገኘበት መኾኑን ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
በ5ኛው የሥራ ቡድን ሥብሠባ ከ19 አባል ሀገራት የተገኘው ድጋፍ በዚህኛው ወደ 30 ሀገራት ማደጉንም ነው የጠቆሙት። ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ጥያቄ ካቀረበች ከ20 ዓመታት በላይ በፈጀው ሂደት ይህ ወሳኝ ምዕራፍ ኾኖ መመዝገቡንም ነው ያብራሩት። የተገኘው ውጤትም ከመቼውም ጊዜ በላይ ለድርጅቱ አባልነት መቃረቧን የሚያመለክት ነውም ብለዋል። የቀጣዩ 7ኛ የሥራ ቡድን ሥብሠባ በመጭው ጥር 2018 ዓ.ም እንደሚካሄድም በመግለጫቸው ጠቅሰዋል።
ዘጋቢ፦ ራሔል ደምሰው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!