“በችግር ውስጥም ኾነው ስኬታማ የኾኑ ተማሪዎች ምሥጋና ይገባቸዋል” ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) 

6

ባሕር ዳር: መስከረም 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በ2017 የትምህርት ዘመን በ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች የእውቅና እና የሽልማት ሥነ ሥርዓት አካሄዷል፡፡

 

በመርሐ ግብሩ መልዕክት ያስተላለፉት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) የእውቅና ሥነ ሥርዓቱ ተማሪዎች በችግር ውስጥ ኾነው በጥረታቸው ላገኙት ውጤት በርቱ ለማለት እና ለቀጣይም እንዲበረታቱ መኾኑን ገልጸዋል፡፡

 

የትኛውም ስኬት በአንድ ጊዜ እንደማይገኝ የገለጹት ዶክተር ሙሉነሽ ተማሪዎች ስኬታቸው የመጨረሻ እንዳልኾነ እንዲገነዘቡ አሳስበዋል፡፡

 

ባለፉት ሦስት ዓመታት የክልሉ ትምህርት በችግሮች እየተፈተነ ይገኛል፡፡ በቀጣይ ብቁ እና ተወዳዳሪ ተማሪ ለማፍራት የሚደረገው ጥረት እንቅፋት እንደሚኾንም ተናግረዋል፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት ትምህርት በእጅጉ መደናቀፉን ዘርዝረው ለክልሉ ሕዝብ የሥነ ልቦና ጫና እንደሚፈጥርም ነው የገለጹት፡፡

 

ባለፉት ሦስት የትምህርት ዘመናት ከግማሽ እና በላይ ውጤት በማምጣት ወደ ዩኒቨርሲቲ መግባት የቻሉት አነስተኛ ቁጥር ያላቸው መኾኑን ነው ዶክተር ሙሉነሽ የገለጹት፡፡

 

በ2017 የትምህርት ዓመት የክልሉ መንግሥት ተማሪዎች የተለየ ዝግጅት እንዲያደርጉ ሥራ መሥራቱን ዶክተር ሙሉነሽ አንስተዋል፡፡ በመኾኑም መሻሻል መታየቱን ገልጸዋል፡፡ ክልሉም በሀገር ደረጃ በሦስተኛ ደረጃ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

 

ከተፈተኑ 94 ሺህ 668 ተማሪዎች መካከል 12 ነጥብ 5 በመቶው ዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ማስመዝገባቸውን ገልጸዋል፡፡ 452 ተማሪዎችም ከ500 እና ከ500 በላይ ነጥብ ማግኘታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

 

ሰባት ትምህርት ቤቶች ያስፈተኗቸውን ተማሪዎች በሙሉ አሳልፈዋል ያሉት ዶክተር ሙሉነሽ ለተማሪዎች ውጤታማነት ከወላጆች ጀምሮ በየደረጃው የሚገኙ አካላትን አመስግነዋል፡፡ አንድም ተማሪ ያላሳለፉ 61 ትምህርት ቤቶች መኖራቸውንም ጠቅሰው ጥብቅ ክትትል እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡

 

ዶክተር ሙሉነሽ ትምህርት የቀጣዩ ትውልድ ሰላም፣ ልማት እና ብልጽግና መሠረት መኾኑን ጠቅሰዋል፡፡ ተሸላሚ ተማሪዎችም በቀጣይ በመተባበር እንዲሠሩ አሳስበዋል፡፡

 

ፈጠራ ሌላኛው ዘመኑ ከተማሪዎቹ የሚጠብቀው መኾኑን አንስተዋል፡፡ ችግሮችን ለመፍታት እና ለማለፍ ዝግጁ መኾን እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡

 

ዓለም አቀፍ ዜጋ በመኾን ሁኔታዎችን መረዳት እና ከሕይወት ጋር አስተሳስሮ መጠቀም ከተማሪዎቹ የሚጠበቅ መኾኑን ዶክተር ሙሉነሽ መክረዋል፡፡

 

ተማሪዎችን በእውቀት፣ በክህሎት እና በሥነ ምግባር ኮትኩቶ በማሳደግ ሀገር ተረካቢ ለማድረግ የወላጆች፣ የመንግሥት እና የባለ ድርሻ አካላትም ኀላፊነት ከፍተኛ መኾኑን አውስተው በቀጣይም ኀላፊነታቸውን ሳይታክቱ እንዲወጡ አደራ ብለዋል፡፡

 

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየባሕር ዳር ከተማን የጎብኝዎች ማዕከል ለማድረግ እየተሠራ ነው።
Next articleለሰላም እጦት ምክንያት የኾኑ የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን በመፍታት ዕቅዶችን ለማሳካት ይሠራል።