
ባሕር ዳር፡ መስከረም 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በ2017 የትምህርት ዘመን በ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች የሽልማት እና ዕውቅና መርሐ ግብር አካሂዷል።
በመርሐ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) የተሰጠው ዕውቅና እና ሽልማት ብቻ ሳይኾን ለተማሪዎች ለነገ የላቀ ትጋት እና ትኩረት የሚሰጥ መኾኑን ገልጸዋል።
ታላላቅ ስኬቶች በታላላቅ ፈተናዎች ውስጥ ይወለዳሉ፤ የእናንተ ውጤትም ችግርን የማሸነፍ እሳቤ ነው፤ ስኬታችሁ ከግለሰብ በላይ ነው ብለዋል።
የአማራ ክልል መንግሥት ትምህርት የሀገር ግንባታ መሠረት መኾኑን እንደሚያምን የገለጹት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ ትምህርት የነገ ሀገር አመላካች መኾኑንም አንስተዋል።
ትምህርት የሀገር ዕድገት እና ብልጽግና የሚተለምበት፤ የሰብዓዊ ልህቀት የሚረጋገጥበት ዘርፍ እንደኾነም ገልጸዋል። ተለዋዋጭ ብዝኅ ችግር ባለበት በ21ኛው ክፍለ ዘመን ዕውቀትን መያዝ ብዙ ዋጋ ያለው ነው ብለዋል። ትምህርት ማኅበረሰብን ከችግር የሚያወጣ እና የሚያሻግር ዘላቂ መንገድ መኾኑንም አንስተዋል።
የአማራ ክልልን የነገ ብልጽግና እና ዕድገት ለማረጋገጥ ዛሬ ላይ የወጣቶችን የትምህርት ልማት በላቀ ደረጃ መምራት ይገባልም ብለዋል።
የክልሉ መንግሥትም የአንድ ትውልድ ዘመን ሕልም እና ርዕይ ቀርጾ የላቀ ሰብዓዊ ልዕልናን ለማረጋገጥ አስተሳስሮ እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
ትምህርት ጥሬ ሀቆችን መማር ብቻ አይደለም ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ከሚሰጥ የትምህርት አማራጭ ሌላ በራስ ጥረትም የሚሳካ ሕይወት መኖሩን አንስተዋል። ዩኒቨርሲቲ ያልገቡትም በሌላ አማራጭ ሕልማቸውን እንደሚያሳኩ እና ለሀገር እንደሚጠቅሙ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
የዛሬ ተሸላሚዎችን የነገ ታላቅ ሰዎች ለማድረግ የወላጆች፣ የመምህራን እና የትምህርት መሪዎች ድርሻ ከፍተኛ እንደኾነ አንስተዋል። ተማሪዎች ውጤታማ እንዲኾኑ ላደረጉ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።
ተሸላሚዎች ነገ የሀገር ችግር ፈቺ እንዲኾኑ አደራ የተሰጣቸው መኾኑን ገልጸዋል። የተጣለባቸውን ኀላፊነት እንዲወጡም አደራ ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!