“የቀይ ባሕር ባለቤቶች”

17
ባሕር ዳር: መስከረም 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ገዢውን ባሕረ ነጋሽ፤ ግዛቱን መረብ ምላሽ እያለች ዘመናትን ኖራለች። ገና ከጥንት ዘመን ጀምሮ በባሕሯ ከሥልጣኔ ላይ ሥልጣኔ ደራርባለች፤ በባሕሯ ከዓለም ቁንጮ የንግድ መዳረሻዎች ቀዳሚዋ ኾናለች፤ በባሕሯ አያሌ መርከቦችን ጭናለች፤ በባሕሯ ወታደሮቿን አስፍራ ሉዓላዊነቷን ጠብቃለች።
ለሙሴ በበትር የተከፈለለት፤ እስራኤላውያን ከባርነት ወደ ምድረ እርስት የተሻገሩበት፤ ፈርኦን ከእነ ሠራዊቱ የጠፋበት፤ ንግሥተ ሳባ በታላቅ አጀብ ያለፈችበት፤ ኃያላን ነገሥታት ኃያል ታሪክ የሠሩበት፤ ቅዱሳን የተመላለሱበት፤ ሥልጣኔ እንደ ጀንበር የደመቀበት፤ ገናና ታሪክ የሚነገርለት ያ ባሕር የጥንታዊቷ ሀገር የኢትዮጵያ ነበር። ይህም ባሕር ቀይ ባሕር ይሰኛል። በዚህ ባሕር ሃይማኖተኞች፤ ነጋዴዎች፣ ሀገር አሳሾች፤ ፖለቲከኞች፤ የጦር አበጋዞች ተመላልሰውበታል። ኢትዮጵያውያን ነገሥታት በቀይ ባሕር አያሌ ታሪኮችን ሠርተውበታል። የውጭ ግንኙነታቸውን በዚሁ ባሕር ላይ አጽንተዋል። የሚመጣውን በወደባቸው ተቀብለዋል። የሚሄደውንም በወደባቸው ሸኝተዋል።
በቀይ ባሕር ላይ የኢትዮጵያ መርከቦች ለዘመናት ተመላልሰዋል። የበዙት ወደቦቿ በመርከቦቿ ተጨናንቀዋል። ነገሥታቱ የባሕር ኃይላቸውን አጠንክረው የሀገራቸውን ሉዓላዊነት አጠናክረዋል። የኢትዮጵያ የባሕር ኃይል አባላት ለዘመናት በጽናት ቆመዋል። ኢትዮጵያውያን ነጋዴዎች በቀይ ባሕር ንግዳቸውን አጧጡፈዋል። ኢትዮጵያ በታሪክ ውስጥ የረቀቀ ስም አላት። ይህ ስሟም ጸንቶ ይኖራል። አንድርዜይ ባርትኒስኪ እና ዮአና ማንቴል ኒችኮ የጻፉት፣ ዓለማየሁ አበበ የተረጎሙት የኢትዮጵያ ታሪክ ከመጀመሪያው እስከ አሁኑ ዘመን በተሰኘው መጽሐፍ እንዲህ ተከትቧል። ኢትዮጵያ እጅግ አስደናቂ እና ልዩ ታሪክ ያላት ሀገር ናት።
በምሥራቁ ዓለም ውስጥ አንዲት ምስጢራዊት ሀገር አለች እየተባለ፤ ገና ከመካከለኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በአውሮፓ ዝናዋ ይታወቅ ነበር፡፡ በዚህ ኹኔታ አያሌ ምዕተ ዓመታት ከተቆጠረ በኋላ፣ ጨለማው ተገፍፎ የሀገሪቱ ትክክለኛ ገጽታ እና እውነተኛ ታሪኳ ሲታይ በወሬ ሲነገር ከኖረው የላቀ ሁኖ ተገኘ። ስንዝር በማያላውሱ የሰሜን ምሥራቅ አፍሪካ ተራራዎች ውስጥ የምትገኘዋ ኢትዮጵያ ብዙ ምዕተ ዓመታት ባስቆጠረው የነጻ መንግሥትነት ታሪኳ ውስጥ አንድ ወጥ ልዩ ሥልጣኔ ፈጥራለች። ከጥቁር አፍሪካ ሀገሮች የሥልጣኔ ክልልም ኾነ በአሕጉሩ ከሚገኙት የዓረብ ሀገሮች የተለየች ናት፡፡
ከኢትዮጵያ ውጭ በዓለም በየትም ሀገር የማይገኘው የጽሑፍ ጥበቧ ለዚህ አንድ ምስክር ነው፡፡ የራሷን ጽሑፍ በማዳበሯና ይህን ያህል ዕድሜ ያስቆጠሩ ቅርሶች ባለቤት መኾኗ ኢትዮጵያን ያለ ጥርጥር ከቀሩት የአፍሪካ ሀገሮች ሁሉ የተለየች ያደርጋታል፡፡ የነጻ መንግሥትነት ፖለቲካዊ ታሪኳ በሀገራዊ ትውፊቱ መሠረት በርከት ያሉ ሺህ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ሰፊው እና ደማቁ ፖለቲካዊ ታሪኳ አንድ ወጥ የኾነው ጥንታዊ ሥልጣኔዋ፣ በአፍሪካ ውስጥ አምሳያ የሌለው ውስጣዊ አደረጃጀቷ እና ከዓለም ውስጥ ከማንኛውም ሀገር ለበለጠ ዘመን ነጻነቷን ጠብቃ የኖረች ሀገር መኾኗ፤ ኢትዮጵያ ያለ ጥርጥር አስደናቂ ከኾኑ ሀገሮች አንዷ እንድትኾን አድርጓታል ተብሎ ተመዝግቧል። ለኢትዮጵያ የሥልጣኔ መድመቅ የቀይ ባሕር አስተዋጽኦ የላቀ ነበር።
የናፓታ እና የመርዌ ሥልጣኔዎች የገነኑት፤ የአክሱም ሥልጣኔ በዘመኑ አቻ ያልተገኘለት፤ ከዚያም ቀጥለው የመጡ ሥልጣኔዎች በዓለም መድረክ የደመቁት ዝም ብለው አልነበረም። ባሕሯን ተንተርሰው በደመቁ ንግዶቿ፤ በሌሎች ዓለማት በማይገኙ ማዕድኖቿ ነበር እንጂ። አምባሳደር ዘውዴ ረታ የኤርትራ ጉዳይ በተሰኘው መጽሐፋቸው ጣልያን አዲስ ስም ከማውጣቱ አስቀድሞ ክፍለ ሀገሩ መረብ ምላሽ፣ የክፍለ ሀገሩ ገዢም ባሕረ ነጋሽ እየተባለ ይጠራ እንደነበርም ይነገራል። ይህ ምድር የኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍለ ሀገር ኾኖ ዘመናትን ተሻግሯል። ከኢትዮጵያ ታሪክም ነጥሎ ማየት አይቻልም። ከክርስቶስ ልደት በፊት በመጀመሪያው እና በሁለተኛው ሺህ ዓመታት ጀምሮ ኢትዮጵያ ከውጭ የሚመጡትን እንግዶቿን ስትቀበል የነበረችው በዚሁ በክፋዩዋ ምድር በኩል እንደኾነ አምባሳደር ዘውዴ መዝግበዋል።
ኢትዮጵያውያን ነገሥታት ሲያንስ እስከ ቀይ ባሕር ያለውን እና ቀይ ባሕርን ጨምሮ፣ ከፍ ሲል ደግሞ ከቀይ ባሕር ማዶ ያለውን ምድርም ይገዙ እና ያሥተዳድሩ ነበር። የጥንታዊው የኢትዮጵያ መናገሻ ከተማ አክሱም እና በአካባቢው የሚገኙ የታሪክ ቅርሶች እና ሐውልቶች የኢትዮጵያን ጥንታዊ ሥልጣኔ ያስረዳሉ። ስለዚህም መረብ ምላሽ ወይም ምድረ ሐማሴን በተባለው የኢትዮጵያ ክፍል የሚኖሩ ወገኖች ለኢትዮጵያዊነታቸው የተለየ ማስረጃ ማቅረብ አያስፈልግም ብለው ጽፈዋል።
የኢትዮጵያ ነገሥታት መንበር ከአክሱም ወደ ሮሃ ላስታ፣ ከላስታ ወደ ሸዋ፣ ከሸዋ ወደ ጎንደር እያለ በተዘዋወረበት ዘመንም የኢትዮጵያ ነገሥታት “ባሕረ ነጋሽ” እየተባሉ በንጉሠ ነገሥቱ በሚሾሙ ታላላቅ ሰዎች ሲተዳደር የኖረ ነው። የቀይ ባሕር ፈተናዎች ቢበዙበትም የኢትዮጵያ ነገሥታት ባሕራቸውን ከመጠቀም አልተመለሱም ነበር። ከበደ ሚካኤል የዓለም ታሪክ በተሰኘው መጽሐፋቸው ኢትዮጵያ የቀደመ ሥልጣኔ ካላቸው ሀገራት ጋር የምተገናኘው በባሕሯ በቀይ ባሕር አማካኝነት እንደነበር ጽፈዋል። የኢትዮጵያ ግዛት ከቀይ ባሕር በመለስ ያለው ብቻ ሳይኾን ከቀይ ባሕር ባሻገር ያለው ሀገርም እንደነበር ጽፈዋል። ኢትዮጵያውያን ነገሥታት ከቀይ ባሕር ባሻገር ላሉ ሕዝቦች ጋሻ እና መከታ እንደነበሩ ታሪክ መዝግቦ አስቀምጧል።
የዚህ ዝግጅት ኢትዮጵያ በዚያ ጊዜ ትልቅነቷ የተመሠረተው በመሬት ጦር ብቻ መኾኑ ቀርቶ በባሕርም ላይ እንደ ነበረ ያስረዳል፡፡
በሪሁን ከበደ የአጼ ኃይለሥላሴ ታሪክ በተሰኘው መጽሐፋቸው ቀይ ባሕር ባሕራችን፣ የአዶሊስ፣ የምጽዋ ወደባችን፤ በባሕራችን ውስጥ የሚገኙት ዳሕላቅ እየተባሉ የሚጠሩት 350 ደሴቶቻችን፤ በባሕሩ ውስጥ ተሞልተው የሚገኙት የጨው እና የዓሣ ሃብታችን ጠላቶች የሚበዙባቸው ናቸው ብለው ጽፈዋል። ጣልያን ኤርትራ ብላ ከመሰየሟ አስቀድሞ ባሕሩን እና የብሱን፣ ወደቡን እና ደሴቱን በአንድ ላይ አጠቃሎ የሚያሥተዳድር ባሕረ ነጋሽ እየተባለ ከጥንት ጀምሮ በኢትዮጵያ መንግሥት የሚሾም ለመኾኑ የታወቀ ነው ይላሉ።
የባሕሩ፣ የምድሩ እና የወደቡ የእርሱ ባለቤት የኢትዮጵያ ነውም ብለው ጽፈዋል። መረብ ምላሽ ጥንት የኢትዮጵያ አካል ነበረች ይላሉ።
ኢትዮጵያ በታሪክ ከታወቀችበት ዘመን ጀምሮ መረብ ምላሽ የኢትዮጵያ አንደኛዋ ክፍል እና አካል ኾና የኖረች መኾኗን ማስረጃ የማያሻው የተረጋገጠ በታሪክ የተመሰከረ ነው። የኢትዮጵያ የሥልጣኔ ምንጮች ከኾኑት ክፍለ ሀገራት አንደኛዋ ናት ብለው ጽፈዋል። ቀይ ባሕር እና መረብ ምላሽ ጠላቶች የሚበዙት ነውና ኢትዮጵያውያን ነገሥታት ሀገሩን ለማደላደል እና ወሰኑን ለማስጠበቅ መስዋዕትነት ሲከፍሉ ኖረዋል። ይህን ሥፍራ አደላድለው ከገዙት ነገሥታት መካከል ደግሞ ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ አንደኛው ናቸው። ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ በመስከረም 24 1945 ዓ.ም መረብ ምላሽን ሊጎበኙ በሄዱበት ጊዜ እንዲህ ብለው ነበር። “ግዛታችንን፣ የባሕር ጠረፋችንን ለመጎብኘት ስንሄድ በመካከል ለያይቶ የነበረው ሰው ሠራሽ ድንበር ተደምስሶ የድንበሩን በር ከፍተን የመረብን ወንዝ በዚህ ሥፍራ ለመሻገራችን መታሰቢያ ለትውልድ ይቆይለት።
ይህ አካባቢ ኤርትራ እየተባለ የተጠራው ከዛሬ 60 ዓመት በኋላ ጀምሮ ነበር። ከዚያ አስቀድሞ ግን ይህ ግዛት ከንጉሠ ነገሥት መንግሥት ግዛታችን ስም ከኢትዮጵያ የተለየ መጠሪያ የለውም ነበር። በአባቶቻችን ነገሥታት ምደረ ሐማሴን ይባል የነበረ ነው” ብለው ነበር። ይህ ምድረ ሐማሴን እና ቀይ ባሕር ከ30 ዓመታት በፊት በስህተት ከመሄዱ አስቀድሞ የኢትዮጵያ መውጫ እና መግቢያ የኾነ የቀደመ እርስቷ ነበር። የኢትዮጵያ የባሕር ኃይል መሠረትም በዚሁ በቀይ ባሕር ነው። ለዚህም ነው ኢትጵያውያን የቀይ ባሕር ባለቤቶች ነን የሚሉት። በሪሁን ሲጽፉ የኢትዮጵያን ክፋይ ባሕረ ነጋሽን ፈርሞ እና አሳልፎ መስጠት እና ማስረከብ የአሁኑንም ኾነ የተከታዩን ትውልድ በጣም የሚያሳዝን፤ ይቅርታ የማይገኝለት ትልቅ የጥፋት ታሪክ ነው ብለዋል። አሁን ከዓመታት በኋላ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን በቀደመው ባሕራችን እንጠቀም ብለው ጠይቀዋል። ስለምን ቢሉ ቀይ ባሕር ባሕራቸው ነውና። ለዘመናት ሥልጣኔን ያረቀቁበት ነውና። በዚህ ዘመን ያስፈልጋቸዋልና። የታሪካቸው አንድ አካልም ነውና።
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleዳውንሲንድረም የሕጻናት ሕመም ምንድን ነው?
Next article“ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ያከናወናቸው የለውጥ ሥራዎች ለተገልጋዩ ኅብረተሰብ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለቸው በተሞክሮነት የሚወሰዱ ናቸው” ፍፁም አሰፋ (ዶ.ር)