“መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የዜጎችን ችግር የሚፈታ ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

25
ባሕር ዳር: መስከረም 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተመርቆ በይፋ ሥራ ጀምሯል።
በማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓቱ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ.ር)፣ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው፣ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት ሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ
መንግሥት የሕዝብ አንገብጋቢ ችግሮች ብሎ ከለያቸው መካከል የአገልግሎት አሰጣጥ አንዱ ነው ብለዋል። ከኋላ ቀር የአገልግሎት አሰጣጥ በመውጣት ዓለም የደረሰበትን ስልጡን አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደኾነም ገልጸዋል። መንግሥት ተግባራትን ወደ አንድ ማዕከል በማምጣት አገልግሎት ለመስጠት ወስኖ እየሠራ መኾኑን አስታውቋል። በአማራ ክልል በሚገኙ ታላላቅ ከተሞች የመሰቦ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ለማስፋት እየተሠራ መኾኑን ነው የገለጹት።
የአንድ ማዕከል አገልግሎት የዜጎችን አገልግሎት የሚያሻሽል፣ ችግራቸውን የሚፈታ፣ ሕዝብን እና መንግሥትን የሚያቀራርብ ነው ብለዋል። ጊዜ ወሳጅ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን በማሳጠር ለዜጎች ውጤታማ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችልም ተናግረዋል። በዜጎች ላይ ይፈጠር የነበረውን የጊዜ እና የጉልበት ብክነት በመቀነስ እርካታቸውን እንደሚያሳድግም ገልጸዋል። ተገልጋዮች መብታቸውን እንዲጠይቁ፣ አገልግሎት ሰጪውም ተጠያቂነት እንዲኖረው ያደርገዋል ነው ያሉት።
በክልሉ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እድገቶችን ለማሳለጥ እንደሚያግዝም ተናግረዋል። በተለይም በኢንቨስትመንት ዘርፉ ውጤታማ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችል ነው የገለጹት። መስቦ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ውጤታማ እንዲኾን መሥራት እንደሚገባም ተናግረዋል። ከአሁን ቀደም የነበሩ የአግልግሎት አሰጣጥ ችግሮች ወደ አንድ ማዕከል አገልግሎቱ እንዳይመጡ መጠንቀቅ ይገባል ነው ያሉት።
ሕዝቡ የሚፈልገው አገልግሎተ በአንድ ማዕከል መኾኑን ብቻ ሳይኾን ውጤታማ እና ቀልጣፋ አገልግሎትን ማግኘት ነው ብለዋል። አገልግሎትን በውጤታማነት መስጠት እንደሚገባም አሳስበዋል። ተገልጋዮች አገልግሎት የማግኘት መብታቸውን እንዲጠቀሙም ጥሪ አቅርበዋል። ተቋማትም ውጤታማ አገልግሎት እንዲሰጡ አስገንዝበዋል።መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እውን እንዲኾን ላደረጉ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።
ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መንግሥት እና ሕዝብን የሚያቀራርብ ነው” ፍጹም አሰፋ (ዶ.ር)
Next articleዳውንሲንድረም የሕጻናት ሕመም ምንድን ነው?