“መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መንግሥት እና ሕዝብን የሚያቀራርብ ነው” ፍጹም አሰፋ (ዶ.ር)

14
ባሕር ዳር: መስከረም 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የአማራ ክልል የአንድ ማዕከል አገልግሎትን መርቀው ሥራ አስጀምረዋል።
በማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ.ር)፣ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው፣ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል። በማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ.ር) መንግሥት ቃል በገባው መሠረት በየደረጃው የሚታዩ የአገልግሎት ጉድለቶችን ለማረም እየሠራ ነው ብለዋል። የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ እና ወደ ልህቀት የሚያሻጋግሩ የአንድ ማዕከል አገልግሎቶች እየሰፉ መኾናቸውን ነው ያነሱት።
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ከፌዴራል ጀምሮ በክልሎች እየሰፋ መኾኑን አንስተዋል። በአማራ ክልል የተጀመረው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትም የዚህ አንዱ አካል መኾኑን ገልጸዋል። እንደ ሀገር ኢትዮጵያን ከኩስመና የሚያወጡ ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውንም አመላክተዋል። የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ፈተና ኾኖ ቆይቷል ያሉት ሚኒስትሯ ይህን ችግር ለመፍታት እንደ ሀገር እየተሠራ ነው ብለዋል። መሰቦ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ሰው ተኮር የአገልግሎት ልህቀትን የሚያረጋግጥ እና ችግሮችን የሚፈታ መኾኑንም አንስተዋል።
መሰቦ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዜጎች የሚፈልጉትን አገልግሎት በአንድ ማዕከል የሚያገኙበት ነው ብለዋል። አሠራሩ መንግሥት እና ሕዝብን የሚያቀራርብ መኾኑንም ጠቁመዋል። በኢትዮጵያ የተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎች ተጨባጭ ውጤቶች ማሳየት መጀመራቸውንም ተናግረዋል። የአገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች የውጤቶቹ ማሳያ መኾናቸውን አንስተዋል።መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን የተስፋ ማዕከል አድርጎ መመልከት እና መጠበቅ እንደሚገባም አሳስበዋል። የፌዴራል መንግሥት የሚጠበቅበትን ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልጸዋል። መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በሌሎች ከተሞችም ማስፋት እንደሚገባ አመላክተዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየጀግኖች ማዕከል ግንባታ በደብረ ብርሃን ከተማ ተጀመረ።
Next article“መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የዜጎችን ችግር የሚፈታ ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ