“በመስቀል ማዕበል ያልፋል፤ በመስቀል መከራ ይታለፋል”

14
ባሕር ዳር: መስከረም 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ክርስቲያኖች ይመኩበታል። ጠላታቸውን ሁሉ ድል ይነሱበታል። የጨለማውን ዘመን አልፈውበታል፤ የመርገምን ዘመን ተሻግረውበታል፤ ሰማይ እና ምድር ታርቀውበታል፤ የሺህ ዘመናት በደል ተደምስሶበታል፤ የረቀቀው ፍቅር ተገልጦበታል፤ ሞት ተሸንፎበታል፤ እስከዘላለምም ድል ተነስቶበታል።
በመስቀሉ ፍቅርን ሰጥቷቸዋል፤ በመስቀሉ ሞትን ሽሮላቸዋል፤ በመስቀሉ ክብርን አውርሷቸዋል፤ በመስቀሉ ኃይልን አድሏቸዋል፤ በመስቀሉ ለዘላለም የማይጠፋውን ብርሃን አብርቶላቸዋል፤ በመስቀሉ በሰው እጅ ያልተሠራውን፣ የማያረጀውን የጽድቅ ካባ አልብሷቸዋል፤ በመስቀሉ አድኗቸዋል። መስቀል ለክርስቲያኖች ምልክታቸው፤ አርማቸው፤ ጌጣቸው ነው። ክርስቲያኖች በአንገታቸው አስረውት ይኖራሉ። በአሠሩት መስቀልም የተከፈለላቸውን ዋጋ፣ የተሰጣቸውን ፍቅር ያስባሉ። መከራውንም ያስታውሳሉ።
ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ለመስቀሉ ካላቸው ፍቅር የተነሳ በአንገታቸው አስረውት አይበቃቸውም። በግንባራቸው፣ በአንገታቸው፣ በእጃቸው ይነቀሱታል።አበው አምላክ ፍጥረታትን፣ የሚታየውን እና የማይታየውን ዓለም ከፈጠረበት ጥበቡ ይልቅ ሰው ኾኖ፣ ሞቶ፣ ዓለምን ያዳነበት ጥበቡ እጅግ ይልቃል፤ ለምን ቢሉ የማይሞት ሞቷልና፤ ሞትን ድል ይነሳ ዘንድ ሞቷልና ይላሉ። ሞትን ድል የነሳውም በመስቀሉ ነው።
በርእሰ አድባራት ወገዳማት ጣና ቅዱስ ቂርቆስ ገዳም የአራቱ ጉባዔያት መምህር ርእሰ ሊቃውንት አባ ገብረኪዳን ግርማ መስቀል ከእግዚአብሔር የማይለይ ፍቅር፣ ረቂቅ ምስጢር ነው ይላሉ። ሰው ከእግዚአብሔር እንዳይለይ የሚጠብቀው መስቀል ነው፤ መስቀሉን ማሰብ የተሰቀለውን ማሰብ ነውና።እርሱ ረቂቅ ምስጢርን በመስቀል ላይ ያሳየ፤ ዓለምን የሚያሳርፍ ነው። መስቀል የክርስቶስ የምስጢሩ መገለጫ ነው ይላሉ።
መስቀል የነፍሳችን ረሃብ የተወገደበት፤ የነፍሳችን ጥም የራቀበት ነው፤ ስለዚህም በመስቀሉ እንመካለን ነው የሚሉት። የመስቀሉ ነገር ለአይሁድ ስንፍና ነው፤ ለእኛ ለምናምን ግን የእግዚአብሔር ኃይል የተገለጠበት ነው። ሞት በዳዊት ወንጭፍ አልተሸነፈም፤ በሙሴ በትርም አልተመታም፤ በሳሙኤል ጦርም አልተወጋም፤ በመስዋዕትም አልጠፋም፤ ሞትን የጣለ፣ ሞትን ያሸነፈ መስቀል ነው ይላሉ።
መስቀል የማይቋረጥ ማዕድ ነውና እንመካበታል የሚሉት ሊቁ መስቀል ዘላለም የሚበሉት ማዕድ ነው፤ ኃይላችን ነው፤ ስለዚህም እንመካበታለን፤ በመስቀል ሞት ተወግዶበታል፤ በመስቀል ጥል ሞቷል ነው የሚሉት። ክርስቶስ በመስቀል ላይ እያለ ዲያቢሎስ ይንቀጠቀጥ ነበር፤ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእሾህ አክሊል ሲደፋበት ለእኛ የብርሃን አክሊል ደፋልን፤ በመስቀል ላይ ሲቸነከር ከእኛ የሀጥያትን ችንካር ያርቅ ነበር፤ በጦር ሲወጋ የሞትን መውጊያ ያርቅ ነበር ነው የሚሉት። በመስቀሉ የሕይወት መብል ተዘጋጅቶልናል፤ በመስቀል የሕይወት መጠጥ ተሰጥቶናል፤ በመስቀሉ ሞት ተሽሮልናል፤ በመስቀሉ ዲያብሎስ ተወግቶ ተጥሎልናል ብለዋል። መስቀል የክርስቶስ መንበሩ ነው፤ መስቀል የሰው እጅ ያልሠራው መቅደስ ነው ይላሉ።
ክርስቶስ በመስቀል የጥል ግድግዳን አፍርሷል፤ በመስቀሉ ሰማይ እና ምድርን አስታርቋል፤ መስቀል የሰላማችን ምንጭ ነው፤ የንስሃ በር የተከፈተልን በመስቀሉ ነው፤ መስቀል ገነት የተከፈተበት ቁልፍ ነው፤ ከመስቀሉ ሥር ቅድስት ድንግል ማርያምን የመሰለች እናትም ተሰጥቶናል ነው የሚሉት። መርከብ እንዳይናወጥ መልሕቅ አለው፤ በመስቀል ያመነው ዓለምም እንዳይናወጥ የክርስቶስ መስቀል አለለት፤ ቤት እንዳይፈርስ መሰሶ ይቆምለታል፤ ቤተክርስቲያን እንዳትፈርስ መስቀል ተተክሎላታል፤ መስቀል ለቤተክርስቲያን መሰሶዋ ነው ይላሉ።
መስቀል የነጻነታችን ምልክት፣ የድላችን አርማ፣ የቤተክርስቲያን መሠረት፣ የረሃብተኞች ማዕድ፣ የተጠሙት ጽዋ ነው፤ ማዕበልን የሚያጠፋው መስቀል ነው ይሉታል። ደመራውን ስንደምር፣ በዓሉን ስናከብር የክርስቶስን ነገር እናስባለን፤ የደመራው እንጨት መስቀል ነው፤ እሳቱ ደግሞ በመስቀሉ ላይ ያለው የክርስቶስ ነበልባል ነው፤ በዚያ የሚያቃጥለው ደግሞ ዲያቢሎስን ነው ይላሉ። የመስቀልን በዓል ስናከብር መታረቅ አለብን የሚሉት ሊቁ መስቀል የእርቅ እንጂ የጠብ በዓል አይደለምና ጥል በፈረሰበት በዓል ላይ ቂም ይዞ ቢያከብሩት ዋጋ የለውም ነው የሚሉት።
የመስቀል በዓል በኢትዮጵያ ከሌላው ዓለም በተለየ ሥርዓት ይከበራል። ስለ ምን ቢሉ ኢትዮጵያ ሃይማኖትን፣ ታሪክን እና እሴትን ጠብቃ የኖረች፤ የትናንቱን ያልተወች፤ ክብሯን በባዕዳን ያልተነጠቀች ናትና። ጠብቃ ኖራለችና ዓለም ሁሉ በአከባበሯ ይደነቃል፤ ይገረማልም።
እነኾ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች የከበሩበትን እያከበሩት ነው፤ ለመመኪያቸው እየሰገዱለት ነው። በመስቀሉ ፍቅርን ያስባሉ፤ በመስቀሉ ድልን ያከብራሉ፤ በመስቀሉ ለዘላለም ይመካሉ ብለዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“የመስቀሉ መገኘት ለዓለም አንድነትን የሰጠ የመዳን ምልክት ነው” ብጹዕ አቡነ በርናባስ
Next article“መስቀሉ የሰላም ምልክት እና የፍቅር አርማ ነው” ብጹዕ አቡነ ሰላማ