የመስቀል ደመራ በዓል በመስቀል ዓደባባይ በድምቀት እየተከበረ ነው።

24
ባሕር ዳር: መስከረም 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የመስቀል ደመራ በዓል በአዲስ አበባ መስቀል ዓደባባይ ሃይማኖታዊ ትውፊት እና ሥርዓቱን ጠብቆ በድምቀት በመከበር ላይ ይገኛል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዓደባባይ በድምቀት ከሚከበሩት በዓላት መካከል የመስቀል ደመራ በዓል በየዓመቱ መስከረም 16 ቀን በመስቀል ዓደባባይ በደማቅ ሥነ-ሥርዓት ይከበራል። በዘንድሮው ክብረ በዓል ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ ብጹዓን አባቶች እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሃይማኖት ተከታዮች ታድመዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የባሕል እና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት አበባ እምቢአለ፣ ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኀላፊዎች፣ የልዩ ልዩ ሀገራት አምባሳደሮች እና ጎብኝዎች ተገኝተዋል። በሥነ-ስርዓቱም በአዲስ አበባ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያንና አድባራት የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን እና ሊቃውንት ሃይማኖታዊ ኅብረ ዝማሬን በማቅረብ በድምቀት እየተከበረ ይገኛል።
የመስቀል ደመራ በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ሃይማኖታዊ እሴት እና ሥርዓታቸውን ጠብቀው በዓደባባይ በድምቀት ከሚከበሩ በዓላት መካከል አንዱ ነው። ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፤ የሳይንስ እና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) የሰው ልጅ ወካይ የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ቅርሶችን ማስመዝገቧ ይታወቃል።
ኢትዮጵያ በዩኔስኮ የማይዳሰሱ ቅርሶች እስከ አሁን ካዝመዘገበቻቸው መካከል የመስቀል ደመራ በዓል አከባበር ሥርዓት፣ ጥምቀት በዓል፣ ፊቼ ጫምባላላ፣ የገዳ ሥርዓት፣ ሸዋል ዒድ እና ሄራ ሂሳ ይገኙበታል። በሚዳሰስ ቅርስነት የተመዘገቡት ደግሞ የሰሜን ተራሮች፣ አክሱም ሐውልቶች፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ የፋሲለደስ አብያተ መንግሥታት ግንብ፣ የታችኛው ኦሞ ሸለቆ፣ ጢያ ትክል ደንጋዮች፣ የታችኛው አዋሽ ሸለቆ፣ ሐረር ጁገል፣ የኮንሶ ባሕላዊ መልክአ ምድር፣ መልካ ቁንጥሬ ባልጩት አርኪዮሎጂና ፓሎአትሮፖሎጂ፣ የጌዴኦ ባሕላዊ መልዕክዓ ምድር፣ ባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ተጠቃሽ ናቸው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየመስቀልን በዓል የቱሪዝም ፍሰቱን በሚጠብቅ ሥርዓት ማክበር ይገባል።
Next article“መስቀል ፍቅር እና አንድነት የተገኘበት፣ ጥል የተሸነፈበት፣ እርቅ የታወጀበት ነው” ብጹዕ አቡነ ሳዊሮስ