“ሕዝባዊ እና ሃይማኖታዊ በዓላት የኢትዮጵያ ብዝኃነት ማሳያ ናቸው” የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት

11
ባሕር ዳር: መስከረም 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት የመስቀል በዓልን አስመልክቶ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል።
በመልዕክቱም ሕዝባዊ እና ሃይማኖታዊ በዓላት የኢትዮጵያ ብዝኃነት ማሳያ ናቸው ብሏል። የመስቀል ደመራ በዓል ኢትዮጵያ በዓለማቀፍ ደረጃ በማይዳሰስ ቅርስነት ካስመዘገበቻቸው መካከል አንዱ መኾኑን ገልጿል። በዓሉ በመላው ኢትዮጵያ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተወራረሰ እና ተጠብቆ የቀጠለ ክዋኔን የሚያሳይ የኢትዮጵያ ብዝኃነት እና ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ማሳያ ነው ብሏል። በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሳይንስ እና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት የተመዘገበውም ይህንን ነባር የአከባበር ትውፊቱን ይዞ እንዲቀጥል፣ ከኢትዮጵያ አልፎ የሰው ልጆች ኹሉ የጋራ ቅርስነቱ እንዲጠበቅ ለማስቻል ነው።
ኢትዮጵያውያንም የመስቀል ደመራ በዓልን በየዓመቱ ጥንታዊነቱንና ማኅበራዊ እሴቱን ጠብቀዉ ያከብሩታል ነው ያለው። መንግሥት ልዩ ትኩረት ከሰጣቸዉ የኢኮኖሚ ዘርፎች አንዱ ለኾነው የቱሪዝም ዕድገትም የራሱን ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል ብሏል። የዘንድሮዉን የመስቀል ደመራ በዓል የምናከብረዉ ደግሞ ኢትዮጵያውያን በጋራ ያሳካነውን የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ድልን እያከበርን ባለንበት ወቅት ነው፡፡ ይህም በዓሉን የበለጠ ደማቅ ያደርገዋል ነው ያለው። እንኳን ለመስቀል ደመራ በዓል አደረሳችሁ ብሏል በመልዕክቱ።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየመስቀል በዓል በሰላም እንዲከበር አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉን የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ።
Next articleእግዚአብሔር ከኛ የሚፈልገው ሰላማዊነትን እና ይቅርባይነትን ነው።