“በመደመር ደመራ እየተመራን፣ በትጋት እየቆፈርን፣ የኢትዮጵያን ብልጽግና እናወጣዋለን” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)

22
ባሕርዳር፡ መስከረም 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ለመስቀል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
እንኳን ለመስቀል በዓል አደረሳችሁ የመስቀል በዓል ሲታሰብ እውነት ተቀብራ እንደማትቀር እናስባለን። መስቀሉ የተቀበረበት ቦታ ተራራ ሠርቶ ነበር። የቀበሩት ሰዎች ከዚህ በኋላ እንደማይወጣ ደምድመው ነበር። አንዳንድ አማኞችም ተስፋ ቆርጠው ነበር። ጊዜው በረዘመ ቁጥር ቀባሪዎቹ ያሸነፉ መስሏቸው ተደሰቱ። የተቀበረው መስቀልም ታሪክ የሆነ መሰለ። ብርቱ ሰዎች፣ እውነት ፈላጊ ሰዎች፣ አቧራውን የሚገልጡ፣ ቆሻሻውን የሚያነሡ ሰዎች፣ ሲመጡ ግን መስቀሉ ከተቀበረበት ወጣ።
እውነት አይቀበርም። ጊዜው ሲደርስ አቧራውን አንሥቶ ዐሻራውን ያሳያል። ሐሰቱን እንደ ጉም አትንኖ፣ ሐቁን እንደ ዐለት አግንኖ ያሳያል።
የኢትዮጵያም እውነት እንደዚሁ ነው። የአውራ ዶሮዎች ጩኸት የፀሐይን መውጣት አያስቀረውም። የሌሊት ወፎች ክንፍ የፀሐይን ንጋት አያግደውም። በዚህም ተባለ በዚያ ፀሐይ ትወጣለች። የኢትዮጵያ እውነት እንደ መስቀሉ ሁሉ አቧራውን ጥሶ፣ አፈሩን አፍልሶ፣ ቆሻሻውን ደርምሶ ይገለጣል። የወጓት ያዩዋታል። ከላይ ሆነው እንዳዩዋት ሁሉ፣ ከታች ሆነው ይገረሙባታል።
በመደመር ደመራ እየተመራን፣ በትጋት እየቆፈርን፣ የኢትዮጵያን ብልጽግና እናወጣዋለን። ይህ ዓመት የኢትዮጵያ ብርሃን ሲወጣ የምናይበት ይሆናል። በድጋሚ መልካም የደመራና የመስቀል በዓል ይሁንልን።
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!
መስከረም 16 ቀን 2018 ዓ.ም
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“መስቀሉ በመስቀለኛ ስፍራ”
Next articleበመስቀሉ ይቅር እንደተባልን እኛም እንዲሁ ይቅር እንባባል።