ምዘናን እያጠናከሩ ውጤታማ ሥራዎችን መሥራት እንደሚገባ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ አሳሰቡ።

18
ባሕር ዳር: መስከረም 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የ2017 በጀት ዓመት የክልል ተቋማት፣ መሪዎች ምዝና ውጤት ግምገማ እና ዕውቅና መድረክ ተካሂዷል።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የምዘና ሥርዓትን እያጠናከሩ ውጤታማ ሥራዎችን መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል። ምዘናዎችን እና የሚገኙ ውጤቶችን አጠቃላይ ከክልሉ ሥራዎች ጋር ማገናዘብ እንደሚገባም አንስተዋል። ምዘናው የሚደረገው የተሻለ ሥራ ለመሥራት እና ክልሉን ውጤታማ ለማድረግ እንደኾነ አስገንዝበዋል። እያንዳንዱ ተቋም የተሻለ ሲፈጽም የተሻለ ክልል መገንባት እንደሚቻልም ገልጸዋል። የምዘና ሥርዓቱን ዘመናዊ ማድረግ እንደሚገባ አመላክተዋል። በሚቀጥሉት ጊዜያት ክፍተቶችን ማስተካከል ጥንካሬዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ነው ያሉት።
የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ፍስሃ ደሳለኝ መመሪያውን መሠረት በማድረግ ተቋማት መመዘናቸውን ገልጸዋል። ትልቅ ሕዝብ የምናሥተዳድር መሪዎች ስለኾንን ሥራዎቻችንም ትልቅ መኾን አለባቸው ነው ያሉት። ምዘና ማድረግ ተቋም እና መሪ ለመገንባት እንደሚያስችል ተናግረዋል። ምዘናውን የበለጠ እያዘመኑ መሄድ እንደሚገባ አንስተዋል። ዋናው ዓላማችን የክልሉን ሕዝብ መጥቀም ነው ያሉት ኀላፊው መነሻ እና መድረሻችን የክልሉን ሕዝብ ፍላጎት ማሟላት እና ጥቅሙን ማስጠበቅ ነው ብለዋል። የሕዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚሠራው ሥራ ደግሞ ጥሩ የፈጸሙ እየተበረታቱ ይቀጥላሉ ነው ያሉት።
በመድረኩ በዓመቱ የተሻለ የፈጸሙ ተቋማት ዕውቅና እና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። በ2017 በጀት ዓመት በነበራቸው አፈጻጸም መሠረት ለዘርፍ፣ ለቢሮዎች፣ ለልማት ድርጅቶች እና ለተጠሪ ተቋማት ዕውቅና ተሰጥቷል። ተቋማቱ የተሰጣቸውን ዕውቅና ከርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ተቀብለዋል።
👉 በዘርፍ ደረጃ የገጠር ዘርፍ በበጀት ዓመቱ የተሻለ በመፈጸም ዕውቅና ተሰጥቶታል።
👉በቢሮዎች
👉 የአማራ ክልል ፕላን እና ልማት ቢሮ አንደኛ ደረጃ
👉 የአማራ ክልል ከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ሁለተኛ ደረጃ
👉 የአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ ተሸላሚ ኾነዋል።
በተጠሪ ተቋማት:-
👉 የአማራ ክልል ኅብረት ሥራ ኮሚሽን አንደኛ
👉 የአማራ ክልል አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ሁለተኛ
👉 የአማራ ክልል እንስሳት እና ዓሳ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት ሦስተኛ በመኾን ተሸላሚ ኾነዋል።
በልማት ድርጅት:-
👉 ዘመን ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን አንደኛ ደረጃ
👉 የአማራ ምርጥ ዘር ሁለተኛ
👉 ኅብር ኮንስትራክሽን ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ ተሸላሚ ኾነዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“የቀጣናው ተሰፋ ሰጭ የሕክምና ማዕከል”
Next articleወርልድ ቪዥን ግብረ ሰናይ ድርጅት 300 ለሚኾኑ ተፈናቃዮች ድጋፍ አደረገ።